ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በማስተዋወቅና በማላመድ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተገለፀ
በጂንካ ዩኒቨርስቲ የተገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ በማከም ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ ምክር ቤት ተጎብኝቷል ።
በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እንደገለፁት የጂንካ ዩኒቨርስቲ ከዩኒቨርስቲው የሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በማከም ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢውን ከብክለት ለመከላከል የተጠቀሙበት ቴክኖሎጂ የሚደነቅ ነዉ ።
የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማልማትና በሌሎች ዘንድ እንዲታወቁ ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርስቲዎች የማህበረሰቡን ችግሮች ከመፍታት አኳያ በርካታ የምርምር ሥራዎች የሚካሄድባቸውና የተማረ ሰዉ ሀይል የሚፈልቁበት መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ ናቸው ።
ትላልቅ ተቋማት በአንድ አካባቢ ሲቋቋሙ ከተቋማቱ የሚወገዱ ቆሻሻዎች በአካባቢውና በማህበረሰቡ ላይ ከሚያስከትሉት ብክለት አንፃር ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል ።
ከሚዲያ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለዩኒቨርሲቲዉም ሆነ ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደሚቻልም ተናግረዋል ።
በዩኒቨርስቲው የአተም አጠቃላይ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮስያስ ብርሃኑ እንደሚሉት ቀደም ሲል ከዩኒቨርስቲው የሚለቀቀው ፍሳሽ ቆሻሻ የአካባቢውን ማህበረሰብና አካባቢውን ለብክለት አጋልጦ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ይሄን ችግር መቅረፍ መቻሉን ገልጸዋል ።ለአጠቃላይ ግንባታው ከ89 ሚልየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል ።
ዘጋቢ: በናወርቅ መንግስቱ-ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
“ለምድራችን ሰላምን በመስበክ በዓሉን ማክበር አለብን” – የሀይማኖት መሪዎች
ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ ነው-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ