የገናና ጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ የህዝብ ፍሰት ከወትሮው የሚጨምር በመሆኑ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 27/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የገናና ጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ የህዝብ ፍሰት ከወትሮው የሚጨምር በመሆኑ ህብረተሰቡ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ።
በዓሉን ከአደጋ ነፃ በሆነ መልኩ ማክበር እንዲቻል ተረጋግተውና የትራፊክ ደንቦችን አክብረው ለማሽከርከር የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።
የሆሣዕና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ኤርቆጮ እንዳሉት የሆሣዕና ከተማ እንደ ክልልም የህዝብ ፍሰት ከሚበዛባቸው ከተሞች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዓላቱን ምክንያት በማድረግ የትራንስፖርት ተገልጋዮች እንዳይጉላሉ ለማድረግ በቂ ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
የታሪፍና ከወንበር ልክ በላይ የመጫን ችግሮችን ለመቅረፍ በሚያስችል ሁኔታ በመናኸሪያዎቹ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትኬት አቆራረጥ ስርዓት መዘርጋቱን የገለጹት ኃላፊው አንዳንድ ከመናኸሪያ ከወጡ በኋላ ጭማሪ በሚያስከፍሉት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አስድተዋል።
አሽከርካሪዎች የፍጥነት ወሰን ጠብቀው ማሽከርከር እንዳለባቸውና ተሳፋሪዎችም ጥንቃቄ በማድረግ ሊከሰት የምችለውን የትራፊክ አደጋን መከላከል አለባቸው ብለዋል።
በሆሳዕና ከተማ አሮጌውና አዲሱ መናኸሪያ የስምሪት ክፍል አስተባባሪ አቶ ንጉሴ መሼ እና አቶ ታደሰ መሳይ በበኩላቸው በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ የአጭር ጊዜ እቅድ በማዘጋጀት ለተሳፋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በአሉን ለማክበር ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የንብረቶቻቸው ደህንነት ተጠብቆላቸዉ መጓዝ እንዲችሉ ከቀይ ለባሾች ጋር በመሆን የተጠናከረ ስራ እየተሰረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
አንዳንድ አሽከርካሪዎች በሰጡት አስተያየት በዓሉን ከአደጋ ነፃ በሆነ መልኩ ማክበር እንዲቻል የትራፊክ ደንቦችን አክብረው ለማሽከርከሩ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በመናኸሪዎቹ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲያገኙ የነበሩ ተሳፋሪዎችም ያለ እንግልት አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ሀዋሳ፡ ታህሳስ 29/2017 ዓ.ም
ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ በተጋጣሚዎቻቸው ተሸነፉ
የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ