በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በብቃት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር የታነፀ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና አመራር አካላት ገለጹ።

ኮሌጁ በ2016 ዓ.ም የስራ ክንውንና በ2017 ዓ.ም ዕቅድና በሩብ አመት አፈጻጸም ዙሪያ ከአመራር፣ መምህራንና የድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የኮሌጁ ዲን አቶ ታደሰ ሀምዳለ እንደገለጹት በዲፕሎማ መርሃግብር የጀመረውን የመማር ማስተማር ሂደት በውጤታማነት እያጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ድግሪ ለሁለተኛ ዙር ለማስመረቅ በማስተማር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደሀገር በጤና ዘርፍ የተነደፈውን ግብ ስኬታማ ለማድረግ ውጤታማ እና ጥራት ያለውን ስልጠና ለመስጠት የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ታደሰ ተናግራዋል።

ኮሌጁ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና መልካም አስተዳደር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሰልጣኝ ተማሪዎች በዕውቀትና ስነ-ምግባር እንዲካኑ ለማስቻል በተለያዩ ሆስፒታሎች የተግባር ተኮር ዕውቀት እንዲቀስሙ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

ኮሌጁ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ መምህራንና ለኮሌጁ ባለድርሻ አካላት ዕውቅና በመስጠት እንደሚያበረታታ የገለጹት አቶ ታደሰ፥ ሌሎችም የእነዚህን አርአያነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተደረገው የዕቅድ ክንውን ምክክር መድረክ ለቀጣይ ክፍተቶችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ ለማስቀጣል ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል።

በኮሌጁ የመማር ማስተማር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድንቁ ዳንኤል በበኩላቸው፥ በሽታን አስቀድሞ በመከላከል ጤንነቱ የተጠበቃ አምራች ዜጋ መፍጠር የሚቻለው በብቃት፣ በክህሎትና ስነ-ምግባር የተካኑ የጤና ባለሙያዎችን በመፍጠር ነው ብለዋል።

ለዚህም ስኬት ኮሌጁ ጥራት ያለውን ስልጠና ለመስጠት የመምህራንን አቅም ማሳደግና የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልጠና በመስጠት እስከ ዶክተሬት ድግሪ እንዲማሩ ማስቻሉንም አቶ ድንቁ ተናግረዋል።

በእለቱ በኮሌጁ በሙያቸው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና በጡረታ ለሚለቁ ሰራተኞች የዕውቅና ሰርትፊኬት፣ የዋንጫና የገንዘብ ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በኮሌጁ በመምህርነትና በተለያዩ ኃላፊነት እያገለገሉ የሚገኙ አቶ ደሳለኝ ግርማ እና በኮሌጁ መምህር ዶክተር ሊቃውንት ሳሙኤል በሰጡት አስተያየት የምክክርና ዕውቅና የመስጠት መድረኩ ለቀጣይ ለኮሌጁ ውጤታማነት እንዲተጉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሌጁ በተለይም የመምህራንን የትምህርት ደረጃ በማሳደግ አቅም መገንባት ላይ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጤና ዘርፍ የሰው ህይወት የመታደግ ጉዳይ በመሆኑ መምህራን በክህሎት፣ ዕውቀትና ስነ-ምግባር የተካኑ የጤና ባለሙያዎችን ለመፍጠር በልዩ ትኩረት ማሰልጠን አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ሳሙኤል መንታሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን