የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድ በሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች ዙሪያ በጂንካ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል ።
በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣የሐይማኖት አባቶች ፣ከሴቶች እና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ የሥራ ሀላፊዎች ፣የሕግ ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮና በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በኩል ጥናታዊ ሰነዶች ቀርበዉ በስፋት ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንደሚሉት በጉዳዩ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ።
በክልሉ እንደ ደቡብ ኦሞ ዞን በርካታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚፈፀሙ በመሆኑ ድርጊቱን ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል ብለዋል።
የሚስተዋሉ ጎጂ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ዘርፈ ብዙ ጫና በጋራ ማወቅ መረዳትና በትብብር መሥራት የተሻለ ዉጤት ለማምጣት እንደሚያስችል የገለፁት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጆሹዋ አየለ ናቸው ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትህ ቢሮ የሕግ ማርቀቅና ማፅደቅ ሥራ ሂደት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይነሽ አበራ እንደገለፁት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ሕግን መሠረት በማድረግ የዜጎችን መብት ማስከበር ይገባል ።
በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ አቶ አያና ጉዲና በበኩላቸው ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራባቸው የሚገቡ በርካታ ጎጂ ድርጊቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ከችግሩ መስፋፋት አኳያ የሁሉንም የተቀናጀ አሰራር የሚሻ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ሰላምነሽ ፍቅሬ-ከጂንካ ቅርንጫፍ

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ