በአርብቶ አደር አከባቢዎች የሴቶች የትምህር ተሣትፎ እያደገ መምጣቱ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መምጣቱ ተገለፀ።
የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ግዛው በወረዳው ከዚህ ቀደም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው፥ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በሴቶች የትምህርት ተሳትፎና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ በተሰሩ የግንዛቤ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል።
በወረዳው በ2017 የትምህርት ዘመን ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከተመዘገቡ አጠቃላይ 6ሺህ 974 ተማሪዎች ውስጥ 2ሺህ 305 ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ከጠቅላላው 33 ነጥብ 5 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
የዳሰነች ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አየለች ኃይሌ ከዚህ ቀደም በወረዳው ሴት ልጆችን እንደ ገቢ ምንጭነት ስለሚጠቀሙባቸው ሴቶችን ማስተማር እንደማይፈልጉ ገልፀው አሁን ላይ ከሀይማኖት አባቶችና የባህል መሪዎች በማስተባበር በተሰራ የግንዛቤ ስራ በርካታ አርብቶ አደር ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እየላኩ እንዳለ ተናግረዋል።
አርብቶ አደር ዎላለይ ቡቡአ፣ ኤሬፌ ኜሩስ እና ኢንጋው ሎኮሮማይ በጋራ በሰጡት አስተያየት የብሔረሰቡ ተወላጅ ሴት ምሁራን የደረሱበት ደረጃ በማየት ከዚህ ቀደም በሴቶች የትምህርት ዙሪያ ያላቸው አመለካከት በመቀየሩ ልጆቻቸውን እያስተማሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ከአርብቶ አደር ሴት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ቻይ ሉቃስ፣ ኦሪፕ አኩዋ እና ሌሎችም እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም በአከባቢያቸው ሴት ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ወላጆች ፍቃደኛ እንደማይሆኑ ተናግረው አሁን ግን በራሳቸውም ሆነ በባለድርሻ አካላት ድጋፍና እገዛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በማስተዋወቅና በማላመድ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተገለፀ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ ነው-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ