ለካሳ ክፊያ ይወጣ የነበረውን 700 ሚሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተማውን ፕላን ለማስጠበቅ እየተሠራ ባለው ሥራ በህብረተሰብ ተሳትፎ 700 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፊያ ይወጣ የነበረውን ማዳን መቻሉን የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አስታውቋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ በመገኘት በከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን ጎብኝቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የ2017 በጀት አመት የመጀመሪያ ዙር ድጋፋዊ ክትትል እና ቁጥጥር ሥራ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ እየተከናወነ ይገኛል።
በጉብኝቱ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ልዑልሰገድ ገመዴ፥ በከተማው በ2017 በጀት አመት አጋማሽ ላይ 30 የወጪ ቁጠባ ቤቶች መገንባታቸው፣ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ደረጃውን የጠበቀ የመማሪያ ክፍል መገንባታቸው እና በከተማ ፕላን ለማስጠበቅ የተሠሩ ሥራዎችን ማየታቸውን ገልጸዋል።
የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስከያጅ አቶ ምንተስኖት ከበደ በበኩላቸው፥ ከተማው ከክልሉ አንዱ ማዕከላት በመሆኑ ከተማውን የሚመጥን ፕላን የማስጠበቅና የኮሪደር ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም፥ አሁን ባለው የከተማ ልማት ሥራ ህብረተሰቡ በራሱ ተነሳሽነት 617 ቤቶችን ያለ ካሳ በማንሳቱ 700 ሚልዮን ብር ከመንግሥት ካዘና ለተነሺ ካሳ ክፊያ ይወጣ የነበረውን ማዳን መቻሉን ጠቁመዋል።
የክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ እንደተናገሩት በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
አክለውም የሚፈለገውን ብልጽግና ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በዲላ ከተማ ላይ እየተደረገ ያለው የህብረተሰብ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በማስተዋወቅና በማላመድ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተገለፀ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ ነው-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ