ዋካን ለማልማት በማንኛውም ተሳትፎ ከከተማዋ አስተዳደር ጎን እንደሚቆም በዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

ዋካን ለማልማት በማንኛውም ተሳትፎ ከከተማዋ አስተዳደር ጎን እንደሚቆም በዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

በ1902 ዓ.ም በኢትዮጵያ በሃገር ደረጃ ከተቆረቆሩ ከተሞች መካከል አንዷ መሆኗ ይነገርላታል የዋካ ከተማ።

ይሁን እንጂ ከተማዋ የዕድሜዋን ያክል ሳትለማ ነው የቆየችው።

የማረቃ ወረዳ አስተዳደሪ ዶ/ር ሀብታሙ ደምሴም ይኸንኑ የሚናገሩ ሲሆን አሁን ግን ጊዜዋ ሆነና እነሆ ከተማዋ በከተማ አስተዳደር መዋቅር ልትታቀፍ ችላለች ነው ያሉት፡፡

ከተማዋ በከተማ አስተዳደር መዋቅር ውስጥ ትግባ እንጂ የሚሉት አስተዳዳሪው፣ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ እስከ ቢሮ ግንባታ ድረስ ገና በርካታ መሟላት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚናገሩት።

ስለሆነም ከተማዋ እንደሌሎች አቻ ከተሞች ሁሉ ተወዳዳሪ እንድትሆን ሁላችንም በምንችለው ሁሉ ዕድቷን በመደገፍ ማፋጠን ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም በወረዳቸው ማረቃ የሚገኙ የመንግስት ስራተኞች፣ ነጋዴዎች፣ አርሶአደሮችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለዋካ ከተማ ዕድገት አጋርነታቸውን እንደሚገልጹ ነው ያረጋገጡት።

ለዚሁም ከወዲሁ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አያይዘው የሚያስረዱት አስተዳዳሪው፤ በቅርቡ ከጥር ሦስት እስከ ስድስት ድርስ በከተማዋ ለሚካሄደው ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር የተሳካ ሆኖ መጠናቀቅና የታቀደውም ገቢም እንዲገኝ የወረዳው ህብረተሰብ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ነው ጨምረው የሚያስረዱት።

በመጨረሻም ለዋካ ከተማ ዕድገት፣ ከማረቃ ወረዳ በተጨማሪ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከዞኑ ውጪም ያሉት ልማት ወዳዶች ከቻሉ በባዛሩ በመሳተፍ፤ ካልቻሉም ለከተማዋ ዕድገት ሲባል ለገቢ ማሰባሰቢያነት በተከፈተው የባንክ አካውንት በተለይ ገንዘብ በማስገባት ድጋፋቸውን እንዲገልፁ ዶ/ር ሃብታሙ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን