የሚዲያ ባለሙያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባር ጠብቀው ማገልገል እንደሚገባቸው ተገለፀ

የሚዲያ ባለሙያዎች ሙያዊ ሥነ ምግባር ጠብቀው ማገልገል እንደሚገባቸው ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለሚዲያ ባለሙያዎችና ኤዲቶሪያል ኮሚቴ የበይነመረብ ጋዜጠኝነትን ያካተተ የዜና አዘገጃጀትና አጠቃቀም ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና በጂንካ ከተማ እየሰጠ ነው።

የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዋስ አቲሳ ባስተላለፉት መልዕክት የጂንካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ13 ብሔረሰቦች ቋንቋ ለሦስት ዞኖች ማለትም ለኣሪ፣ ለደቡብ ኦሞና ለኧሌ ዞኖች የሚዲያ ሽፋን እየሰጠ መሆኑን ገለጸው፥ የሚዲያ ባለሙያዎች የመረጃ ልውውጥን ለማጉልበት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስለሰጠው ምላሽ አመሰግነዋል።

ስልጠናው የሚዳያ ባለሙያዎች ማህበረሰቡ የሚፈለገውን መረጃ በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጋር በመተባበር አቅምን የሚገነባ ስልጠና መሆኑንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተድላ ሆራ ምክር ቤቱ ከተቋቋመ አራት ዓመት ዕድሜ ያለው ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ከአንድ መቶ በላይ ጋዜጠኞችን ያቀፈ ድርጅት ሆኗል ብለዋል።

አቶ ተድላ አክለው ምክር ቤቱ በዋናነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የጋዜጠኞችን አቅም ማጎልበትና ሚዲያዎችን በቴክኒክና በተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው የእርስ በርስ ቁጥጥርን ጨምሮ በጋዜጠኞች ነጻነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከሚዲያ ተቋማት ጋር አፅንኦት ሰጥተን እየሰራ ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በጂንካ ከተማ የተጀመረው የሚዲያ ባለሙያዎች ስልጠና ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በሠላም ጋዜጠኝነትና በጋዜጠኝነት ሥነምግባር ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ተመላክቷል።

ዘጋቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን