ከአጠቃላይ የአይን ህክምና ባለፈ የእይታ መዛባት ላይ ያተኮረ ህክምና ላይ መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከአጠቃላይ የአይን ህክምና ባለፈ የእይታ መዛባት ላይ ያተኮረ ህክምና ላይ መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስተር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል ገለፁ።

“ONE SIGHT ESSILOR LUXOTICA FOUNDATION (OSELF)” ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአይን እይታ ችግር፣ ህክምናና የመነጽር አቅርቦት ማዕከላትን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።

የመነጽር አገልግሎትን ጨምሮ የአይን እይታ ግድፈቶች ህክምና መስጫ ማዕከላት በዞኑ በአምስት የጤና ተቋማት የተሰናዳ ሲሆን በቦኖሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎቱ በይፋ ተጀምሯል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት ኢሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ይድነቃቸው ደዳቸው እና የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በመርሀግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር በሆስፒታሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የታካሚዎች ቁጥርና አገልግሎቱን ለማመጣጠን እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የህክምና አገልግሎቱን በማዘመን በአገልግሎት ፍላጎት፣ በጥራት፣ በተደራሽነትና በመድሃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ለዚህም በፋውንዴሽኑ በኩል በአይን ህክምናው ዘርፍ የተደረገው ድጋፍ አጋዥ ነው ብለዋል።

በወቅቱ ተገኝተው የህክምና አገልግሎቱን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስተር ዴኤታ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሌሊሳ አማኑኤል አገልግሎቱን ከማዘመን አንጻር እንደሌሎቹ የህክምና ዘርፎች ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰው፥ የዓይን ህክምና ዘርፍ አሁን በተሰጠው ትኩረት በቀጥታ የዓይን ህክምና ዘርፍ ላይ መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ከአጠቃላይ የአይን ህክምና ባለፈ  የእይታ  መዛባት ላይ ያተኮሩ  ህክምናዎች አሁንም ትኩረት የሚያሻቸው ናቸው ያሉት ዶክተር ሌሊሳ፥ ፋውዴሽኑ ዘርፉን መደገፉ የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፥ በኢትዮጵያ ደረጃ በአምስት ክልሎች የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲያሰፋ ጠይቀዋል።

ፋውንዴሽኑ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚሰራ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ በ22 ሀገሮች እንደሚሰራ የገለፁት ደግሞ በዋን ሳይት ኤሴሎር ላክሶቲካ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ አቶ ዘለቀ አለሙ ናቸው።

በመነጽር ሊስተካከሉ የሚችሉ የዓይን ችግሮች ላይ በማተኮር አገልግሎት የሚሰጥባቸው ተቋማትን በማጠናከር፣ የባለሙያዎችን ክህሎት በስልጠና በማሳደግ፣ መነጽር በማቅረብና መነጽርን ለመስራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ላይ ፋውንዴሽኑ በዋናነት እንደሚሰራም አሳውቀዋል።

የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ዶክተር ደሳለኝ ሽጉጤ በበኩላቸው የዓይን እይታ ችግሮች ላይ መስራት የሚቻልባቸው ማዕከላት በፋውንዴሽኑ ድጋፍ  በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት ኢሌኒ መሐመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ   ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ በሻሾጎ፣ በሶሮ፣ በሌሞና በግቤ ወረዳዎች ስራ መጀመራቸው በማህበረሰቡ የአይን ጤና ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

በዕለቱም የሆስፒታሉን የአይን ጤና ህክምና ማዕከል ጨምሮ የተለያዩ የህክምና ዘርፎች የስራ እንቅስቃሴ ተጎብኝቷል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን