ሀዋሳ፡ ታህሳስ 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተጠና የመስኖ ስራ በመስራት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ገለፀ።
ኤጀንሲው በሀላባ ዞንና በቀቤና ልዩ ወረዳ ሊገነቡ የታቀዱ የግድብ ስራዎች የጥናት ቅድመ አዋጭነት ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ ኢ/ር ካሳዬ ተክሌ እንደተናገሩት በበጀት ዓመቱ በስድስት ወራት ውስጥ በጥናትና ዲዛይን፣ በግንባታ እንዲሁም በተቋማት አስተዳደር ሰፉፊ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
በሀላባ ዞንና በቀቤና ልዩ ወረዳ ሊሰሩ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ቅድመ አዋጭነት ከክልሉ ጥናትና ዲዛይን ቁጥጥር ቢሮ በጋራ በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ግምገማ በማካሄድ ስራው ከሚሰራበት ቦታ ካሉ ማህበረሰብ ጋር በመወያየት ተግባራዊ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የሚሰሩ ስራዎች ህዝብ ያመነባቸው እንዲሆኑ ፕሮጀክቶቹ የሚሰሩበት ቦታ ያሉ መዋቅሮች በውይይቱ እንዲሳተፉ በማድረግ መግባባት እየተፈጠ መሆኑን አስገንዝበዋል።
አቶ እስማኤል ወራጌ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው የጥናቶቹ ግምገማ በቀጣይ በተሳካ ሁኔታ ስራዎችን ለማስፈጸም እድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥናቱም የማህበረሰቡን ፍላጎት መመለስ የሚያስችል ነው ያሉት ስራአስኪጁ፥ ውጤታማ በሚያደርግ ቦታ የተመረጠ መሆኑንም በጥናቱ መመልከት ተችሏል ነው ያሉት።
የፕሮጀክቶች መጓተት እንዳይኖር ጥናቶች ወሳኝ ናቸው ያሉት አቶ እስማኤል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በመደረጉ ውጤታማነቱ የተሻለ ይሆናል ብለዋል።
በኤጀንሲ የጥናትና ዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሙጎሮ በበኩላቸው ግድቦቹ በሚሰራባቸው ቦታዎች ከፍተኛ የውሃ ችግር በመኖሩ አስፈላጊውን በማከናውን ሀይቆችን የመፍጠር ስራ ለመስራት በየመዋቅሩ ያሉ አመራሮች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ከዞንና ከልዩ ወረዳ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት የተጠኑት ኘሮጀክቶች የአርሶአደሩን የማምረት አቅም የሚጨምሩ በመሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
የመስኖ ጥናቱ ባመላከተበት ቦታ ውስን ባለይዞታዎች የሚነካ በመሆኑ ከባለይዞታዎቹ ጋር በመወያየት ልማቱን ማፋጠን ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡ አስረስ ንጋቱ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች ከተጠቃሚነታቸው ባለፈ በፈጠራ ስራቸው ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆነ ተገለጸ
በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ተቋማት ጋር የመረጃ ግንኙነት በማጠናከር በሁሉም ዘርፎች የህብረተሰቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ
የገና ሰሞን በጉራጌ !!!