ሀዋሳ፡ ታህሳስ 22/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሐንስ የተመራ ልዑክ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በመገኘት እየተሠሩ ያሉ እና ያልተጠናቀቁ ካፒታል ፕሮጀክቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ በ2005 ዓ.ም የከፈታ ሥራ ተጀምሮ በተያዘለት ጊዜ ሣይጠናቀቅ ቆይቶ በ2015 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን የዲላ ዲስትሪክት በራሱ ተቋራጭ በአዲስ መልክ የተጀመረው ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ቡላ ቀበሌ ተነስቶ አራት ቀበሌያትን የሚያገናኝ የማነ አምባ የ24 ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራ እና ለበርካታ ዓመታት የህብረተሰቡ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የባንቲስቡ ቀበሌ ድልድይ ምልከታ ተድርጓል።
የመንገድ ሥራ በተያዘለት ጊዜ ባይጠናቀቅም በ2015 በጀት አመት የዲላ ዲስትሪክት በራሱ ተቋራጭ ሥራ አስጀምሮ በተሻለ ደረጃ ላይ መኖሩን እና የድልድዩ መዘግየት የህብረተሰቡ ችግር ሆኖ ከመቆየቱ ባሻገር የመንገድ ሥራንም እያጓተተ በመሆኑ በሚፈታበት ሂደት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ በክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ መሠረተ ልማት እና የመንግስት ሃብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሐንስ በዚሁ ወቅት ተናግረዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ እና የገጠር መንገድ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፍቃድ ጥላሁን እንደተናገሩት፤ በዞኑ የገጠር መንገድ ተደራሽነት 62 በመቶ ነው።
አክለውም በቀጣይ የዞኑን ህብረተሰብ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት በዞኑ በርካታ አካባቢዎች የመንገድ ዝርጋታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉብኝቱ በቀድሞው ክልል የተጀመረው ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ቡላ፣ ወቻማ፣ ባንትሲቡ እና ካላቻ ቀበሌያትን የሚያገናኝ የመንገድ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን የዲላ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሃኢየሱስ ካሣዬ ተናግረዋል።
መንገዱ ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ቡላ ቀበሌ ተነስቶ አራት ቀበሌያትን የሚያገናኝ አጠቃላይ 24 ኪሎ ሜትር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ 12 ኪሎ ሜትር መንገድ በመጠናቀቁ በቀጣይ ቀሪ ስራዎችን በተያዘው በጀት አመት ለማጠናቀቅ እንደሚሠራም አቶ ፍስሃኢየሰሱ ገልጸዋል።
ካነጋገርናቸው የዲላ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጀቦ ደጎማ እና አቶ ተስፋዬ አላኮ የባንቲስቡ እና የአምባ ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ፤ መሠል የሚደረጉ ጉብኝቶች መንግሥት ከህዝብ ጋር በቅርበት እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን በመግልጽ የረዥም ጊዜ ችግር ሆኖ የቆየው ከቡላ-ካላቻ መንገድ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት እስኪጀምር የክትትል ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የዘንድሮው የጌዴኦ ብሔር የዘመን መለወጫ ዳራሮ በዓል በተለያዩ ኩነቶች መከበር ጀመረ
በእንስሳት እርባታና በጓሮ አትክልት ሥራ በመሰማራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን በወላይታ ዞን የአረካ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች ገለጹ
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተደራጁ ወጣቶች ከተጠቃሚነታቸው ባለፈ በፈጠራ ስራቸው ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆነ ተገለጸ