የማህበረሰቡን ነባር መልካም ባህላዊ እሴቶች ለአገር ሠላምና አንድነት ካላቸዉ አስተዋፅኦ አንፃር መጠበቅና ለትዉልድ ማሸጋገር ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅ ሀላፊነት መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

የማህበረሰቡን ነባር መልካም ባህላዊ እሴቶች ለአገር ሠላምና አንድነት ካላቸዉ አስተዋፅኦ አንፃር መጠበቅና ለትዉልድ ማሸጋገር ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጠበቅ ሀላፊነት መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳደር አስታወቀ

በዞኑ ማሌ ወረዳ ጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚከበረው የማሌ ብሔረሰብ መዘን መለወጫ “ዶኦሞ” በዓል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የማሌ ብሔረሰብ በየዓመቱ ጥር 01 ቀን የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ “ዶኦሞ” በዓል ከበርካታ እሴቶቹ ሠላም፣ አንድነትና መተማመን ተጠቃሽ እንደሆኑ የገለፁት የብሔረሰቡ ተወላጅና የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ናቸው።

የዘንድሮው የማሌ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ዶኦሞ” በዓል ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች እንዲደምቅ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

የብሔረሰቡን ማንነት የሚያደምቁ በርካታ ነባር መልካም ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለትዉልድ ለማሸጋገር በቅንጅት እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

የማህበረሰቡን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን መልካም ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት በማስቀጠል በተናጠልና በቡድን ሲያከብሩት የቆዩትን እሴቶቻቸውን መንከባከብ እንደሚገባ የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሰ ገልጸዋል።

የተለያዩ የመልካም እሴቶች ባለቤት የሆነው “ዶኦሞ” በዓል ባለፈውን ዓመት ያጋጠማቸዉን ተግዳሮቶች ባህላዊ ሥርዓቶችና ደንቦችን በመከወን መሻርና አዲሱ አመት መልካም ተግባራትን የሚያከናዉኑበት ጊዜ እንዲሆንላቸው የሚዘጋጁበት እንደሆነም ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ደግነሽ አልቆ በበኩላቸው፤ በየደረጃው አዲሱን ትዉልድ በመልካም ሥነ-ምግባር በማነፅ የቀደሙ አባቶችን ጠቃሚ እሴቶች የማጠናከር፣ የመንከባከብና የማስቀጠል ስራ እየተሰራ መሆኑን ነዉ የገለፁት፡፡

ጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም በድምቀት በሚከበረው የማሌ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ዶኦሞ” በዓል ላይ በቅርቡም በሩቁም የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ወዳጆች በመታደም አብሮነታቸዉን እንዲያጠናክሩ የወረዳዉ አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል፡፡

ዘጋቢ፡ ማማዬ ዲማኮ – ከጅንካ ጣቢያችን