ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ

ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሱቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በዩኒርሲቲው የቋንቋ፣ የባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል በአዲስ መልክ መደራጀትን አስመልክቶ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደጥናት እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ቋንቋና ባህላዊ እሴቶች እንዲሁም የሀገር በቀል ዕውቀቶች ባለቤት መሆኗን ገልፀዋል።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የማህበረሱቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር እያደረገ የሚገኘው ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የቋንቋ፣ የባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል በአዲስ መልክ መደራጀትን አስመልክቶ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ለዘርፉ ውጤታማነት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አመላክተዋል።

በአውደጥናቱ ላይ በባህልና ሀገርበቀል ዕውቀት፣ የጉራጊኛ ቋንቋ አጭር ዳሰሳ፣ የቀቤና ባህላዊ ዳኝነት ስርአት፣ የየም ባህላዊ መድሃኒት፣ ጀፎረን የተመለከቱና ሌሎችም ጥናታዊ ፅሁፎች በምሁራን እንደሚቀርቡ ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እና የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊልን ጨምሮ ከፌደራል፣ ከክልሉ፣ ከጉራጌና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች፣ ከቀቤና ልዩ ወረዳና ከየም ዞን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችና ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ መሀመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን