የኢኮኖሚ አቅምን ያገናዘበ የቤተሰብ ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ደስተኛ ህይወት ለመምራት እንደሚያስችል በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የህዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚ አቅም ጋር ለማመጣጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደሩ አስታውቋል።
ወ/ሮ ውቢት ደንቢና አቶ ናሆም ነጋ የይርጋጨፌ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሻለ የቤተሰብ ህይወት እንዲመሩ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
የኢኖኮሚን አቅም ያላገናዘበ ህይወት የሚያስከትሉ ድርብ ጋብቻ፣ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎትን በተገቢው መንገድ አለመጠቀምና መሰል ችግሮች እንዲቀረፉ የሚጠበቅባቸውን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የከተማው ፕላንና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አየለ የከተማው ህዝብ ብዛት ከዓመታት በፊት ከነበረበት በፍጥነት በማደግ አሁን ላይ 130 ሺህ 178 መድረሱን ገልፀው ለዚህም ከገጠር ወደ ከተማው ከሚደረገው ፍልሰት ባለፈ የቤተሰብ ዕቅድ በተገቢው ሁኔታ አለመተግበር መሆኑን ጠቁመው በየዓመቱ የህዝብ ዕድገት ምጣኔ 4 ነጥብ 9 መሆኑን ገልጸዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ጽ/ቤቱ ለተለያዩ ኅብረተሰብ ክፍሎች የውይይት መድረክ በማዘጋጀት፣ ቤት ለቤትና በሚዲያ መረጃ ተደራሽ በማድረግ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ሥር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት መሥራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የከተማው ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን በበኩላቸው በየጊዜው እያደገ ያለውን የከተማውን የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት ለማሟላት የማስፋፊያ ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከተማውን ወደ 2ሺህ 557 ሄክታር በማስፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት ከመሥራት ጎን ለጎን በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ ከኢኮኖሚ አቅም ጋር ለማመጣጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስተዳደሩ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በየት/ቤቶች ባሉ ሥነ ህዝብና ሥነ ተዋልዶ ክበባት አደረጃጀቶች በኩል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ የመለወጥ ሥራ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የጠቆሙት ከንቲባው፥ የባህልና ሐይማኖት አባቶች እንዲሁም በየደረጃ ያለ አመራሮችና ባለሙያዎች ችግሩን ለመቅረፍ እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ከንቲባው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በማስተዋወቅና በማላመድ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተገለፀ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ ነው-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ