የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለፀ፡፡

የልዩ ወረዳዉ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ጎሮ ወረዳ እና ከጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ አጎራባች ህዝቦች ጋር በሰላም ዙሪያ የዉይይት መድረክ አካሂዷል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ የህብረተሰቡን ሰላም እና ደህንነት በዘላቂነት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ በዘላቂ ሰላም ግንባታ ዙሪያ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር እየተሰራ ባለዉ ቅንጅታዊ ስራ ህብረተሰቡ ሊያግዝ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የጎሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተማም ኑርሃሳ፤ ከጥንት ጀምሮ በአብሮነት የኖሩ ህዝቦች አንድነታቸዉን ለማጠናከር ባለፉት አመታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የህብረተሰቡን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላት ከአጎራባች የመንግስት መዋቅር ጋር እየተሰራ ባለዉ ቅንጅታዊ ስራ ተጨባጭ ለዉጦች መምጣታቸዉን በመግለፅ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አብድልወሃብ ከማል በበኩላቸዉ፤ ልዩ ወረዳዉ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በሰላም ዙሪያ እያካሄደ ባለዉ የዉይይት መድረክ በቀጠናዉ ሰላም መስፈኑን አመላክተዋል።

ሰላሙን በዘላቂነት ለማስቀጠል የፀጥታዉ መዋቅር ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር ሙህዲን ነጋሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን የተለያዩ የህዝብ መድረኮች በመፍጠር እየተሰራ ይገኛል። ይህንን ለማጠናከርም ከአጎራባች መዋቅሮች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም እንዳለበት በመግለፅ በሁሉም መዋቅሮች እየተደረጉ ያሉ የሰላም ዉይይቶች ዉጤታማ መሆናቸዉን አመላክተዋል። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።

በመድረኩ ከቀቤና ልዩ ወረዳ፣ ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የጎሮ ወረዳ እና ከጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙሂዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን