የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የኤችአይቪ ቫይረስ ጫናን ለመግታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ አካሂዷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ጋርሾ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለበሽታው እየተሰጠ ያለው ትኩረት እየቀነሰ በመምጣቱ ስርጭቱ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው በ2030 በሽታውን ለመከላከል የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ለኤችአይቪ ከተመረመሩ 93 በመቶ ለሚሆኑት የአባላዘር በሽታ ምርመራ መደረጉን የሚገልፁት አቶ ማቴዎስ፤ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የጉበት ቫይረስንም ለመከላከል እየተሠራ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ለስርጭቱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍልና ወጣቱ ላይ የግንዛቤ ሥራን በማጠናከር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሊሠራ ይገባልም ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት መልካ እንደገለፀት፤ እንደሀገር የተቀመጠውን ለመተግበር በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ምንተስኖት አክለውም በየደረጃው ካሉ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ከመሥራት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን በማረም ከክልል ጀምሮ በተዋረድ ያሉ መዋቅሮች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የቫይረሱን ስርጭት ሊከላከሉ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ የጤና ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙና ለቀጣይ ሥራቸው ተጨማሪ አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በ2030 ኤች አይ ቪ ቫይረስ የጤና ስጋት እንዳይሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የደም ምርመራ፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት በመጠቀምና የግንዛቤ ሥራን በማጠናከር በአግባቡ ሊመራ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ከማህበራዊ መሠረት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን