የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን ገለጹ።

የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመደበኛ እና በተከታታይ ትምህርት መርሐ ግብር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለ16ኛ ዙር በደረጃ 4 ያሰለጠናቸው 547 ተማሪዎችን አስመርቋል።

ኮሌጁ በዚህ ለ16ኛ ዙር ባካሄደው የምረቃ ሥነስርዓት ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 241 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንም ተመላክቷል።

የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አብዱልዋሂድ መሃመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ለደረጃው የሚመጥን ዕውቀት ፣ ክህሎትና አመለካከት በመጨበጥ እንዲሁም በምዘና በማረጋገጥ ለምረቃ በቅተዋል ብለዋል።

ኮሌጁ በ1990 ሰራ መጀመሩን ያወሱት ዲኑ በ2016/17 የትምህርት ዘመን በ27 የሙያ ዘርፎች እና በ12 የትምህርት ክፍሎች 1ሺህ 198 ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ ከዘርፉ ዋነኛ ተልዕኮዎች መካከል ገበያን፣ ተግባርን፣ ጥራትንና አግባባዊነትን ታሳቢ ያደረገ ስልጠና በስታንዳርዱና በሳይንሳዊ መንገድ በመስጠት አዳዲስ እሳቤዎችን ተግባር ላይ እያዋለ ይገኛል ነው ያሉት።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሃሰን የሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረ የቡታጅራ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅም ይህንኑ በውጤታማነት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በሃገሪቱ ለዘርፉ የተሰጠው ተልእኮ ክህሎት ስራ ፈጠራ እና ገበያ ተኮር የስልጠና ሂደት ስርኣት እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ዘርፎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ስለሆነም በዞኑ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው በሚደረገው እንቅስቃሴ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች የተጣለባቸው ትልቅ ሃላፊነት እንዲወጡ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሀላፊ አቶ አሰፋ ደቼ እንዳሉት  የምረቃ ጊዜ የትምህርት ጉዞ መጨረሻ ብቻ ሳይሆን አዲስና ተጨባጭ ህይወት የመጀመር ጊዜ በመሆኑ ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ማህበረሰቡን ለመለወጥና ሃገሪቱን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም እንዳላቸው  ተናግረዋል ።

በመሆኑም ይህን ችሎታ ከልምድ ጋር በማጣመር ተግባር ላይ በማዋል ቴክኖሎጂን ለመቅረጽ እና ችግሮችን ለመፍታት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አመላክተዋል ።

የእለቱ ምሩቃን ሰልጣኞችም በተሻለ ውጤት መመረቃቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው ይህም ጠንክረው ከሰሩ በችግር ውስጥ ታልፎ ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በኮሌጁ የተሰጣቸው ስልጠና በቂ እውቀትና ክህሎት እንዳስጨበጣቸው ገልጸው በቀጣይም ስራ ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸው ስራ ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- መሃመድ ሽሁር