ምዝበራንና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት የኦዲት ስራን በይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል- የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ጸሀይ ወራሳ
የ2017 በጀት አመት የኦዲት ግኝት ክትትልና ቁጥጥር ግብረ ሀይል የ6 ወር አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከናውኗል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ እንዳሉት በኦዲት ረገድ ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ።
በዚህም መሻሻሎች ቢኖሩም አሁንም የኦዲት ግኝት ተመሳሳይ መሆን፣ አዳዲስ የኦዲት ግኝት በአንዳንድ ተቋማት ላይ መታየት ፣ ባልተሟላ ሰነድ ክፍያ መፈጸም፣ የተሰብሳቢና የተከፋይ ሂሳብ ማበጥና ሌሎች የኦዲት ግኝቶች መኖራቸው በይበልጥ ሰፊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል።
የኦዲት ሪፖርት በወቅቱ ተደራሽ ከማድረግና ለክዋኔና ለአከባቢ ኦዲት ግብረ መልስ ከመስጠት አንጻር ሰፊ ውስንነት የሚታይ መሆኑንና በተገኙ የኦዲት ግኝቶች መነሻነት ተጠያቂነትን ከማስፈን አኳያ የሁሉንም ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የግብረ ሀይሉ ሰብሳቢ ወ/ሮ ጸሀይ ወራሳ በመድረኩ እንዳሉት በየጊዜው የአሰራር ስርአትና ደንቦች ባለመጠበቃቸው የመንግስትና የህዝብ ሀብት ለምዝበራ የተጋለጠ በመሆኑ ጠንካራ የኦዲት ቁጥጥር አግባብ ሊኖር ይገባል ብለዋል።
የተጠያቂነት መርህ አለመጠናከር በየጊዜው አዳዲስ የኦዲት ግኝቶች እንዲፈጠሩ በር ከፍቷል ያሉት ወ/ሮ ጸሀይ ያለንን ውስን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የአሰራራር ጥሰትን በማስቀረት የሚስተዋለውን ክፍተት ማረም እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በመድረኩ በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኢንስፔክሽንና የውስጥ ኦዲት ዘርፍ የጥሬ ገንዘብና የአፈር ማዳበርያ ዕዳ የኦዲት ግኝት ሪፓርት የቀረበ ሲሆን በዚህም የገንዘብ ዝውውርና የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ላይ የሚታይ ውስንነት መኖር ክፍያዎችን ያለ ዋስትና መስጠት የተፈቀደ በጀት ሳይኖር ክፍያ መፈጸም የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተነስቷል።
እንደዚሁም የ 1 ቢሊዮን 481ሚሊዮን 591ሺህ 167 ብር የአፈር ማዳበርያ እዳ በኦዲት ግኝት የተጣራ መሆኑንና 99 ሚሊዮን 347ሺህ 423 ብር የተመለሰ ሲሆን ያልተመለሰ ቀሪ እዳ 1 ቢሊዮን 382 ሚሊዮን 243 ሺህ ብር በኦዲት ግኝት መኖሩ ታውቋል።
በክልሉ ም/ቤት የመሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሀንስ ባቀረቡት ሪፓርት የኦዲት ቁጥጥር ስራን ለማጠናከር በየደረጃው አቅም የመገንባት ስራና የጠራ መረጃ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ቁጥጥሩን በባለቤትነት የመከታተልና ተቋማዊ አሰራርን የማስፈን ተግባርን ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ በ2015 ዓ.ም የከፋ የኦዲት አስተያየት ያገኙ 17 ፋይናንስ ተቋማትና የአምስት አመት የዞኖች ኦዲት ግኝት ለመድረኩ ያቀረቡ ሲሆን እንደ ክልል የታየውን የ11 ቢሊየን የተሰብሳቢ ሂሳብ ማሰረጃ ካለ ቀርቦ እንዲወራረድ ፣ ማሰረጃ መቅረብ የማይቻል ከሆነ ጥሬ ገንዘብን ወደ መንግስት ካዝና በመመለስ በኦዲት ግኝት ላይ የእርምት ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዘጋቢ ፡ ማርታ ሙሉጌታ-ከአርባ ምንጭ ጣቢያዎች
More Stories
የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እየተሰሩ ያሉ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ
የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ተጎጂዎች በስምንት ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ