የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብረሰናይ ድርጅቶች ሚና የጎለ እንደሆነ ተገለፀ

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብረሰናይ ድርጅቶች ሚና የጎለ እንደሆነ ተገለፀ

ቢቢቢሲ የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ እየሰራ ያለው ስራ ተጨባጭ ለውጦችን ያስገኘ እንደሆነ ተመላክቷል።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገና በሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው “ቢቢቢሲ” የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ከ50 አመታት በላይ የቆየ ሲሆን በሀዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ አገልግሎቱን ከጀመረ 10 አመታትን አስቆጥሯል።

ወ/ሮ ብርቅነሽ ሽፈራው በወረዳው ዱባንቾ ቀበሌ የራስ-አገዝ የሴቶች ልማት ማህበር ላይ የልዕልሴ ቡድን አስተባባሪ ሲሆኑ፤ በፕሮጀክቱ አማካይነት በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ታግዛው ገንዘብ በመቆጠብ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ዛሬ ላይ የተሻለ ገቢ መምራት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ስራውን ከመጀመሩ አስቀድሞ በሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ላይ በርካታ ክፍተቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ወ/ሮ ብርቅነሽ፤ በጤና አጠባበቅ፣ በትምህርትና በሌሎችም መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ የመጡ ለውጦች ከራሳችን አልፈን ለሌሎች አርአያ እንድንሆን አግዞናል ነው ያሉት።

የፕሮጀክቱ ዋና አላማ ሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማብቃት እንደሆነ ነው የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዲታ ታደሰ የተናገሩት።

በተለይም በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የመጡ ለውጦች የፕሮጀክቱን ራዕይ ያሳካ እንደነበርም አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ ጅምር ላይ በወረዳው በ4 ቀበሌያት የጀመረውን ስራ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የወረዳውን ቀበሌያት ማዳረስ መቻሉን ያረጋገጡት አቶ አብዲታ፤ በቀጣይም በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ ተደራሽነትን የማስፋት ዕቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱን ተደራሽነት ከፍ በማድረግ በጉራጌ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እንደተደረገም ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ በጤና፣ በትምህርትና በልማት ስራዎች የሴቶችን ንቁ ተሳትፎ ከማረጋገጥ ባሻገር ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እራሳቸውን የመከላከል ግንዛቤ ያገኙበት እንደሆነ የተናገሩት አቶ አብዲታ፤ በተለይ ከመንግስት ባለድርሻ አካላት በተናበበና በተቀናጀ መልኩ መስራት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን አስረድተዋል።

በወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ ክፍሌ፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብረሰናይ ድርጅቶች ሚና የጎለ እንደሆነ ተናግረዋል።

በ”ቢቢቢሲ” በተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት አማካይነት በተሰራው ስራ በሴቶች ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ የመጣው ለውጥ ሴቶች ከራሳቸውና ከአካባቢያቸው አልፎ ለሀገራዊ ለውጥ እንዲያስቡ የሚያስችላቸውን ስብዕና እንዲላበሱ አድርጓቸዋል ነው ያሉት አቶ መንግሥቱ።

በዚህም የጋራ መድረኮችን በተለያዩ ጊዜያት በመፍጠርና በጋራ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት አቶ መንግሥቱ፤ ይህም በሁሉም መስኮች ላይ የመተጋገዝ ስራዎችን በማጠናከር የታየ ስኬት ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡ አለቃል ደስታ – ከሆሳዕና ጣቢያችን