ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ተቀራርቦ በጋራ መሥራት በተለያየ ጊዜ የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ በኮሬ ዞን የኬሌ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አስተዳደር በተጀመሩ የልማት ሥራዎችና በከተማዋ ዕድገት ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የጋራ ውይይት ተካሂዷል።

በኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ በተሠሩ በርካታ የልማት ሥራዎች ላይ የማህበረሰቡና በተለይ የነጋዴዎች ሚና ቀላል የማይባል መሆኑን የጠቆሙት የኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  ዮሐንስ ኃይሉ ሲሆኑ፥  ለከተማዋ ዕድገትና ልማት መደማመጥና አብሮ መሥራትና መተጋገዝ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለከተማዋ ዕድገት እንቅፋት የሚሆኑ የፀጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ስጋት የሚፈጥሩትን ማስወገድ ቀጣይነት ላለው የከተማ ልማትና ዕድገት አስፈላጊ እንደሆነ በማስመር ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ከመድረኩ በስፋት ተነስቷል።

በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል ዳይና ክሌ ክምቦ፣ አቶ አሸናፊ አፍሮ እና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት በከተማ ልማት ዙሪያ ለመነጋገርና ኃላፊነታችንን ለመወጣት በመገናኘታችን ደስተኞች ነን ሲሉ ነው የተናገሩት።

ታታሪነታችንና ጥንካሬያችንን በማስቀጠል የኬሌ ከተማን ዕድገት ለማፋጠን ሁላችንም በሀሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ መደገፍ አለብን ነው ያሉት።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የንግዱ ማህበረሰብ በኬሌ ከተማ ሊሠሩ ለታቀዱ የተለያዩ የልማት ሥራዎች የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተው መድረኩ ተጠናቋል ።

ዘጋቢ: ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን