ሀዋሳ፡ ታህሳስ 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በክልሉ ለሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የማስተማር አቅም ግንባታ ዙሪያ በሣውላ ከተማ ስልጠና እየሰጠ ነው።
ስልጠናው በሥራና ተግባር ትምህርት አሠጣጥ ዙሪያ የመምህራንን ክህሎት በማሳደግ አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የትምህርት ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ታምራት ይገዙ ጠቁመዋል።
የትምህርት ስብራትን በመጠገን በአዲሱ ትምህርት ፖሊሲ መነሻ ለመምህራን ተጨማሪ አቅም በመገንባትና የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
ዶ/ር ታምራት አክለውም ቢሮው የትምህርት ተደራሽነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ብቃትና ጥራትን ለማስጠበቅ የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥራና ተግባር ትምህርት አፈጻጸም ላይ በክልሉ ወጥነት ያለው አፈጻጸም አለመኖሩን የት/ት ቢሮው የሥርዐተ ትምህርት ዝግጅትና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዘርፍ ኃላፊ ተወካይ አቶ ተመስገን ቶማስ ባቀረቡት ገለጻ ጠቁመው፥ ክፍተቱ በተለይ የተማሪውን ዝንባሌና የአካባቢውን የመልማት አቅም አስተሳስሮ ከማስኬድ አኳያ እንደሆነም ገልጸዋል።
የሥራና ተግባር ትምህርት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ሲደረግ ቆይቷል ያሉት አቶ ተመስገን በሞያ ዘርፍ ብቻ የሰለጠኑ መምህራን የማስተማር፣ የክፍል ውስጥ የተማሪና አሰተማሪ ግንኙነት እውቀታቸውን ለማሳደግ ያለመ ሥልጠና መሆኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በኮሪደር ልማት፣ የመንገድ ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የጠቅላላ ተቋራጮች እና የአገልግሎት ተቋማት ትጋትና ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ
በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማህበራዊ ጫናዎችን ለመከላከል የኢኮኖሚ ባለቤት እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለፀ
ትምህርት ቤቶች የዉስጥ ገቢያቸዉን በማሳደግ የግብዓት ችግሮችን በመቅረፍ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢን መፍጠር እንዳለባቸዉ ተገለፀ