በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ገለጸ

በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ በዞን መዋቅር ሥር የሚገኙ ባላድርሻ አካላት በተገኙበት በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት የተሠሩ የተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ግምገማ መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር)፤ በዞኑ የሚገኙ አመራሮች በመሠጠት፣ ወቅታዊ ሁኔታን በመረዳት እና ዕቅዶችን በመተግበር ሥራቸውን መፈጸም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ተግባር የሚጀምረው ከልየታ እስከ ትግበራ ድረስ የሚከናወን ተግባር መሆኑን የተናገሩት አስተዳዳሪው፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በመፍታት ለሥራ አጥ ወጣቶች ክህሎት መር የሥራ ዕድል ለመፍጠር የዞኑ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ፣ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ እና ሌሎች አቻ የመንግስት ተቋማት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዞኑ ቴክኒክ እና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ አካሉ ሐልቻዬ እንደተናገሩት፤ በ2017 ዓ.ም በዞን ደረጃ ባሉ አራት የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ከደረጃ አንድ እስከ አምስት 2 ሺህ 74 ሠልጣኞችን ለመቀበል አቅደው 9 መቶ 21 ሠልጣኞችን መመዝገባቸውን ገልጸው ከዕቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ አናሳ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንደሠሩ ገልጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ለ52 ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ በተሠራው ሥራ ባለፉት አምስት ወራት በዞን ደረጃ ከሰባት ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚ እና ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ ተናግረዋል።

የዞኑ ሠራተኞች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬነሽ ሮባ እንደተናገሩት፤ ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ከዕለት ጉርስ የዘለለ ሥራ ፈጥረው ከእራሳቸው አልፈው አካባቢያቸውን እንዲያሻሽሉ እና ለሀገር ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ መምሪያው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን