የወራቤ ማረሚያ ተቋም የታራሚ አያያዝና አደረጃጀት በተገቢው መንገድ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

ቋሚ ኮሚቴው የወራቤ ማረሚያ ተቋም በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

በተቋሙ በጊዜ ቀጠሮ ላይ ያሉትን ጨምሮ በጥቅሉ 934 ታራሚዎች እንደሚገኙ የወራቤ ማረሚያ ተቋም ሀላፊ ኮማንደር አወል ሁሴን ገልጸዋል።

በተቋሙ የሚገኙ ታራሚዎች የቀለም ትምህርት እንዲከታተሉ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ትምህርት ቤት መኖሩን፣ ጽዱና ምቹ መጠለያ፣ የእደ ጥበብና መሠል ሙያ ሰልጥነው እንዲሰሩ መደረጉንም አስታውቀዋል።

እንደ ኮማንደር አወል ገለጻ ታራሚዎችን በማህበር በማደራጀት በከብት ማድለብ፣ በፍየልና በግ ማሞከት እንዲሰማሩና የገቢ ማግኛ መንገዶች ከማመቻቸት ባለፈ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል።

በማረሚያ ተቋሙ የህግ ፍርደኞች አያያዝና ጥቅል አደረጃጀት የሚደነቅ መሆኑን ነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሠረት ወልደሰንበት የተናገሩት።

ተቋሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን እያዘጋጀ ለአካባቢው ማህበረሰብ በነጻ በማቅረብ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ወደፊትም የገቢ ምንጭ ማድረግ እንዲሁም ተግባራቱም በዘርፉ ባለሙያዎች ተደግፎ መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።

ዘጋቢ፡ አብደላ በድሩ