ዲጂታል ኢትዮዽያን ለመፍጠር በሚሰጠው ሀገራዊ የኢ-ኮዲንግ ስልጠና ተሳትፎና ተግባራዊነት ከማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የጉራጌ ዞን አፈፃፀም ከፊት እንደሚገኝ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ገለፁ

ዲጂታል ኢትዮዽያን ለመፍጠር በሚሰጠው ሀገራዊ የኢ-ኮዲንግ ስልጠና ተሳትፎና ተግባራዊነት ከማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የጉራጌ ዞን አፈፃፀም ከፊት እንደሚገኝ የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ገለፁ

ስልጠናውን ያልወሰዱ ዜጎች ከዲጂታል አለም የውድድር ስርዓት ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉም የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ አስታውቋል::

ኢትዮዽያና ኢትዮዽያውያንን ወደ ዲጂታል ዓለም ለመቀላቀል በጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና በተባበሩት አረብ ኤምሬት መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቨ ተፈጥሮ 5 ሚሊየን ወጣቶችን ለማሰልጠን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወሳል:: በዚህም የኢ-ኮዲንግ ስልጠና በ4 የተለያዩ የኢ-ኮዲንግ መስኮች ስልጠና መሰጠት ከተጀመረ ጊዜያት ተቆጥረዋል::

በጉራጌ ዞን በሚገኙ የስልጠና ማዕከላት ተገኝተው ሰልጣኞችን የተመለከቱት የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደተናገሩት፤ ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነች ዲጂታል ኢትዮዽያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ወጣቶች የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል::

በዚህ የተግባር አፈፃፀም እንደ ማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል የጉራጌ ዞን ተሳትፎና ተግባራዊ ማጠናቀቅ ከፊት እንደሚገኝ ጠቅሰው በአካል ተገኝተው በተመለከቱት ተግባር መደሰታቸውን ተናግረዋል::

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ፣ የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ሳተላይት ኮሌጅ ዲንና የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ምክትል ዲን በበኩላቸው በስልጠናው ተሳታፊ ያልሆኑ ዜጎች ከዲጂታል አለም የውድድር መድረክ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተው ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል::

በጉራጌ ዞን በተለያዩ የስልጠና ማዕከላት ስልጠናቸውን የጀመሩና ያጠናቀቁ ሰልጣኞች የኢ-ኮዲንግ ስልጠና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው እውቀት እንዳስጨበጣቸው በመጠቆም የነጋቸውን ተስፋ ብሩህ እንዳደረገላቸውም ጠቁመዋል::

የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢፎ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ፤ በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ዩኒቨርስቲ፣ የያበሩስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የአገና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠና ማዕከላት ሰልጣኞች በአካል ተገኝተው በመመልከት ለሰልጣኞች አነቃቂ ምክረ ሃሳብ ለግሰዋል::

ዘጋቢ፡ መሐመድ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን