የበጋ መስኖ ልማት ተግባር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚያደርገው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የሀድያ ዞን አስተዳዳር ገለጸ

ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ የመንገድ ችግር መኖሩ ለውጤታማነታቸው ማነቆ እንደሆነባቸውና መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የአካባቢው አርሶ አደሮች ጠይቀዋል።

የዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሻሾጎ ወረዳ በቢዲቃ ቀበሌ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ፤ በዞኑ የመኸር እርሻ ምርት አሰባሰብ የተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች ወደ በጋ መስኖ ልማት ተግባር መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

በሻሾጎ ወረዳ ቢዲቃና በጀሎ አዳነቾ ቀበሌያት የታየው የመስኖ ልማት ተግባር ለሌሎች አካባቢዎችም ተሞክሮ እንደሚሆን አመላክተዋል።

የሀድያ ዞን ስንዴ የማምረት አቅም ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው የተጀመረውን የበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት በማልማት ምርቱን ከፍጆታ ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ሀብታሙ ታደሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዞኑ ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን ከዚህም 6.6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የበጋ መስኖ ተግባር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የገቢ ምርትን ለመተካት ሚናው የጎላ እንደሆነም አብራርተዋል። በዘርፉ የግብዓት እጥረት እንዳይገጥም ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።

በወረዳው 3 ሺህ 9 መቶ 95 ሄክታር ማሳ በበጋ መስኖ ለማልማት መታቀዱን የገለፁት የሻሾጎ ወረዳ ግብረና ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ወንዱ መለሰ ናቸው።

ከዚህ ጎን ለጎን የቢዲቃና የጀሎ አዳንቾ ቀበሌ አጠቃላይ የመስኖ ልማት ስራዎች ጉብኝት ተደርጓል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጀመሩት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት በኑሯቸው መሻሻል መነሻ እየሆነ መምጣቱን አርሶ አደሮቹ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ምርቱን በስፋት ማምረት እንዲቻል የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍ የጠየቁት አርሶ አደሮቹ፤ በተለይም ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ የመንገድ ችግር መኖሩ ለውጤታማነታቸው ማነቆ መሆኑን አንስተዋል።

ምርቱ በተገቢው ለገበያ መቅረብ እንዲችል የመንገድ ችግር ለማስተካከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ማቴዎስ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን