በዳውሮ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ የምክክር  መድረክ  ተካሄደ

በመድረኩ በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የወከሉ የህዝብ ተወካዮችና ባለድርሻዎች የተገኙ ሲሆን፣ የወባ በሽታ   በዞኑ በወረርሽኝነት ደረጃ ላይ የሚገኝ  መሆኑ  በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስራት ቸርነት እንደተናገሩት፣ የወባ በሽታ ዞናዊ የስርጭት መጠኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየተባባሰ መገኘት ለመድረኩ  መዘጋጀት ምክንያት ነው።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት ኃላፊው በሽታውን ከመከላከልና ከመቆጣጠርም አንፃር ያለውን ተቋማዊ ስራ ውጤታማ ለማድረግ ህዝባዊ መሠረትን ማስያዝና መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመድረኩ ዞናዊ የወባ በሽታን መከላከልና ስርጭት ዙሪያ አጠቃላይ ገለፃና ማብራሪያ በዞኑ የጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስዮም ከበደ ለታዳሚዎች የቀረበ ሲሆን  ውይይት ተደርጎበታል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ የወባ በሽታን የመከላከልና መቆጣጠሩን ስራ ውጤታማ ለማድረግ በዘርፉ ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ እስከ ማከም ባለው የባለድርሻዎች ቅንጅትና ትርጉም ያለው ተሳትፎ በዞኑ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዞኑ ያለው የዘርፉ መረጃ እንደሚያመለክተውም በዞኑ ዳውሮ ካለው የህዝብ ቁጥር ወደ 482ሺህ 523 የሚጠጋው ለወባ በሽታ ተጋላጭ ሲሆን፣ ይህም በመቶኛ ሲቀመጥ ከአጠቃላዩ የህዝብ ብዛት 65 በመቶውን የሚይዝ መሆኑ ተመላክቷል።

በመድረኩ ላይ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከተለያዩ ህዝባዊ መሠረት ካላቸው አደረጃጀቶች የተገኙ  የማህበረሰብና የቤተ እምነት ተቋማት መሪዎች፣ ከየደረጃው ምክር ቤቶች የተገኙ አፈ ጉባኤዎችና ሌሎችም ተገኝተውበታል።

ዘጋቢ፡ ወግደረስ አማረ – ከዋካ ጣቢያችን