በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ በኮረሪማ ምርት ከሚለማው 8ሺህ 860 ሄክታር መሬት 50ሺህ ኩንታል ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

የወረዳው አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት የኮረሪማ ምርት የተሻለ ገቢ እንዲገኙ የገበያ ትስስር ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

አርሶ አደር ደነቀ ጎሹ በመሎ ኮዛ ወረዳ ቶባ ቀበሌ ሞዴል የኮረሪማ አምራች ሲሆኑ በመኖሪያ ቤት ዙሪያ ከሚያመርተው ውጪ ከ7 ሄክታር በላይ መሬት ኮረሪማ ብቻ በማልማት በየዓመቱ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ሌላኛው የኮረሪማ አምራች አርሶ አደር አርሼ ዘለቀ በበኩላቸው፤ በኩትኳቶና በአረም ወቅት የሚወገዱ ቅጠላ ቅጠሎችን በኮረሪማው ማሳ ውስጥ መልሰው እንዲበሰብሱ በማድረግ እንደ ማዳበሪያ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግም የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

ኮረሪማ ከተተከለ ከ3 እስከ 5 ዓመት ቆይቶ ምርት መስጠት እንደሚጀምር የገለጹት የቀበሌው አርሶ አደሮች ምርት መስጠት ከጀመረ በኋላ ከ7 እስከ 10 ዓመታት በየአመቱ ከ1 ሄክታር በአማካይ ከ30 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ አመላክተዋል።

አርሶ አደሮቹ በአካባቢው በክረምት ወራት ከፍተኛ የመንገድ ብልሽት የሚያጋጥም መሆኑን አንስተው በዚህ ሳቢያም የምርት ብልሽት እንደሚያጋጥማቸው ጠቁመዋል።

አክለውም ከሚያመርቱት የኮረሪማ ምርት የተሻለ ምርት ገቢ እንዲያገኙ የገበያ ትስስር ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።

የመሎ ኮዛ ወረዳ ግብርና ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሙላቱ መኮንን በበኩላቸው፤ በወረዳው በመጪው ሚያዝያ ወር የሚካሄደውን ተከላ ሳይጨምር 8ሺህ 860 ሄክታር መሬት በኮረሪማ ምርት መልማቱን ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ 50ሺህ ኩንታል የኮረሪማ ምርት እንደሚቀርብ የገለጹት ኃላፊው ለመጪው ሚያዝያ ወር ከ10ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለተከላ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ወረዳው በቅመማ ቅመምና ፍራፍሬ ምርት የሚታወቅ በመሆኑ አርሶ አደሩ በሚያመርተው ምርት ብልጽግናውን እንዲያረጋግጥ እየተሰራ እንደሚገኝ የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤልያስ ገልጸዋል።

ከመንገድና ገበያ ትስስር ረገድ አርሶ አደሮች ላነሱት የመፍትሄ ጥያቄ በተያዘው አመት ከዞኑና ከክልሉ መንግስት እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመስራት እንደሚፈታም አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን