ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የካፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ለ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ቤት ቀርበዉ እንዲመዘገቡ ወላጆች የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስቧል።
በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከ350 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ዝግጅት ማድረጉንም መምሪያዉ አስታዉቋል።
የመምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መሸሻ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ከቦንጋ ጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በሁሉም አካባቢዎች የ2018 ትምህርት ዘመን ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ተማሪዎችን ለምዝገባ እየተጠባበቅን ነዉ ብለዋል።
በዞኑ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በሚገኙ 643 ትምህርት ቤቶች 351 ሺህ 458 ተማሪዎችን በመመዝገብ የ2018 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ ለመጀመር የሚያስችሉ ስራዎች መጠናቀቃቸዉንም አንስተዋል።
በዚህም ምዝገባ ከነሐሴ 19/2017 ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚከናወን ገልጸዉ፤ ወላጆች ልጆቻቸዉን በጊዜ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ እንዲያስመዘግቡም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በዞኑ በፓይለት ደረጃ በተመረጡ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች የአንድ ቀን ምዝገባ ስራ ነሐሴ 16/2017 ዓ/ም በይፋ መጀመሩንም አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።
የመማር ማስተማር ስራዉ ስኬታማ መሆን እንዲችልም በክረምት ወቅት የመማሪያ ክፍሎችን ማሟላት፣ የትምህርት ቤት ግብአቶችንና የግቢ ማጽዳትና መሰል እንቅስቃዎች እየተከናወኑ መቆየታቸዉን ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ በአሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለረጅም አመታት በፀጥታ ችግር ያለማውን የማዕድን ሀብት በመጠቀም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማጂ ወረዳ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ
በአካል ጉዳተኝነት ተስፋ ባለመቁረጥ የተገኘ ስኬት
ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ