በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ የምሁራን ምክክር ተካሄደ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ወረዳዊ አንድነት ለጋራ ህልሞቻችን ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የምሁራን ምክክር ተካሂዷል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አይዴ ሎሞዶ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማህበረሰቡን በተደጋጋሚ እየደረሰበት ካለው ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በመታደግ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የወረዳው ምሁራን ሀሳባቸውን አደራጅተውና አንድነታቸውን አጠናክረው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በወረዳው ያሉ ሶስት የመስኖ ተቋማትን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ በማድረግ የሚቀርቡ እርዳታዎችን እና የእንስሳት ኢንሹራንስ ገንዘብ በአግባቡ ለታለመለት አላማ በማዋል አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ አመራሩና ምሁራኑ በመቀናጀት መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደሰ ጋልጶክ በበኩላቸው፤ አመራሩና ምሁራኑ በጋራ ተቀራርበው በመወያየት የአርብቶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከውሃ ሙላት ጋር ተያይዞ በማህበረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቅረፍ በቀጣይ ከፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅለት ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ፤ ለአርብቶ አደሩ መልካም ስራ ለመስራት ከአመራሩ ጋር በጋራ በመቀናጀትና አንድነትን በማጠናከር የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በስፖርትና ባህል ልማት ዘርፍ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አበክሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ
ህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የክልሉን ፍትህ ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ሥራ አፈፃፀም አደመጠ
ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እንደሚሠራ የዲላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ