ምክር ቤቱ አረንጓዴ አሻራን የሚያጠናክር እና የተጎሳቆለ መሬትን እንዲያገግም የሚያስችል አዋጅ አፀደቀ

ምክር ቤቱ አረንጓዴ አሻራን የሚያጠናክር እና የተጎሳቆለ መሬትን እንዲያገግም የሚያስችል አዋጅ አፀደቀ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባው አረንጓዴ አሻራን የሚያጠናክር እና የተጎሳቆለ መሬትን እንዲያገግም የሚያስችል አዋጅ አፅድቋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 26/2016ትን በተመለከተ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጀውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ የአዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ አዋጁ በሀገራችን የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በደን ልማት እና በጥምር ደን ግብርና መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ‐ምህዳራዊ ጠቀሜታ ይሰጣል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉና ወደፊት የሚተከሉ ችግኞች ቀጣይነት ባለው መልኩ፣ በቋሚነት እና በተቀናጀ አግባብ የፌደራል መንግስት የበጀት ድጋፍ የሚያደርግበት እንዲሆን፣ ክልሎችም የበኩላቸውን ድጋፍና አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ሀገራችን በደን ዘርፍ ከልማት አጋሮችና ከሌሎች ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ሰጪ ምንጮች እና ከካርበን ግብይት ስርዓቶች የምታገኘውን ድጋፍና ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መሆኑንም ነው አቶ ደሳለኝ ያብራሩት፡፡

የምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ከነማሻሻያዎቹ አዋጅ አድርጎ እንዲያፀድቀውም ሰብሳቢው ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት የቀረበው አዋጅ እንዲፀድቅ የድጋፍ ድምፅ የሰጡ ሲሆን፤ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በቀረበው አዋጅ ላይ በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡

በቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የአቶ ደሳለኝ ወዳጆ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በቀረበው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን፤ አዋጅ ቁጥር 1361/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ መፅደቁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘገባ ያመላክታል፡፡