የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ጥላሁን ከበደ መልዕክት
እንኳን ለ”ማሮ” የባኔ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሰን! አደረሳችሁ!
በብዝኃነት የተዋበው ኅብረ-ብሔራዊው ክልላችን፤ የየራሳቸው የጊዜ ቀመርና የዘመን መለወጫ በዓላት ያሏቸው ሕዝቦች መገኛ ነው፡፡
ማሮ የባኔ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል፤ በህዝቡ የጊዜ ቀመር መሠረት በወርሃ ታህሳስ አጋማሽ በድምቀት የሚከበር የምስጋና በዓል ነው፡፡
ባህላዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ የሚከበረው፤ አሮጌውን ዓመት በምስጋና ሸኝተው፤ አዲሱን ዓመት በብሩህ ተስፋ በመቀበል በጋራ ማዕድ የሚቀመስበት፤ የተቸገሩ የሚረዳዱበት የመተሳሰብ እና የአብሮነት በዓል ነው፡፡
ማሮ በባኔ ህዝብ ዘንድ አሮጌውን ዓመት በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረገ ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብና መጪው አዲስ ዘመንም የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የበረከት እንዲሆን በምርቃት አዲሱን ዓመት የሚቀበሉበት ነው፡፡
በዓሉ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገሩ በመጡ፤ የህዝቡን አብሮነትና አንድነት በሚያጠናክሩ የ ‘ዞምቢያሽካ’ እና የ ‘ደንዛሞ’ ባህላዊ ስርዓቶች፤ የተጣሉ ዕርቅ አውርደው፤ አዲሱን ዓመት በኢባንጋዲ ጨዋታ ታጅበው በደስታና በአብሮነት የሚያከብሩት ድንቅ የክልላችን እሴት ነው፡፡
የሰላም፤ የአንድነትና የመደጋገፍ እሴቶችን ባቀፉ ባህላዊ ክዋኔዎች የታጀበው የማሮ በዓል፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ከነሙሉ ባህላዊ እሴቱ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም አባቶች ያቆዩልንን ይህን ድንቅ እሴት፤ የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት የበዓሉን ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ እሴቶችና ክዋኔዎች ሰንዶ ለማሻገር መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር

More Stories
ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ፣ የዕጩ ማስተዋወቂያ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራም በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ አካሄደ
ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የአይን ህክምና በሀገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
ብልጽግና ፓርቲ የማህበረሰቡ ችግር የሚቀርፉ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ በማጠናቀቅ በውጤታማነት ለአገልግሎት እያበቃ ነው – ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ