በ2017 በጀት ዓመት ከ3 መቶ ሺ በላይ አዲስ አባላትን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል – የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሆሳዕና ክላስተር

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ2017 በጀት ዓመት ከ3 መቶ ሺ በላይ አዲስ አባላትን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ አባወራና እማወራዎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሆሳዕና ክላስተር አስታወቀ።

ሁሉም ህብረተሰብ በወቅቱ አባል በመሆንና የአባልነት መዋጮ በመክፈል የጤና ዕክል ሲያጋጥመው በጤና ተቋማት ላይ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳለበትም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሆሳዕና ክላስተር በማዕከላዊና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ 162 ወረዳዎችንና ከተማ አስተዳደሮችን የሚያጠቃልል መሆኑን የሆሳዕና ክላስተር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ምህረተአብ ዋሚሾ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት በዋናነት ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንና የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ያሉት ኃላፊው፤ ዋና አላማውም አምራች፣ ጤናማና የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር መሆኑንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በገንዘቡ ልክ ሳይሆን በህመሙ ልክ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በ2016 በጀት አመት 772 ሺህ 860 አባወራና እማወራዎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ማድረግ የተቻለ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመትም 3 መቶ ሺህ አዲስ አበላትን ለመጨመር ታቅዶ በሁሉም መዋቅሮች የንቅናቄ መድረኮች መደረጉን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ እስካሁን በክላስተሩ ከ4 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ማድረግ እንደተቻለም አቶ ምህረተአብ ጠቁመዋል።

በጤና ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የመድሀኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በየጊዜው ውይይቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸው ያነሱት ኃላፊው፤ በተለይ የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ መንግስት የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን እያደራጀ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል በመሆን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም የጤና ዕክል ሲያጋጥማቸው እስከ ከፍተኛ ሆስፒታሎች ድረስ  በመሄድ አገልግሎቱን እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል ለመሆን የመክፈል አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በመንግስት በኩል የሚሸፈንላቸው መሆኑንም አቶ ምህረተአብ ገልፀዋል።

ወቅቱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባልነት አዲስ ምዝገባ የሚካሄድበት እና የነባር አባልነት ዕድሳት የሚደረግበት እንደመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ በየመዋቅሩ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን