በቀቤና ልዩ ወረዳ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸዉን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በተያዘዉ በጀት አመት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ገለፀ

በቢሮዉ ሀላፊ በአቶ ዳዊት ሀይሉ የተመራዉ ቡድን በቀቤና ልዩ ወረዳ በበጀት አመቱ የሚገነቡ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ስፍራዎችን የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ በክልሉ ተጀምረዉ ያልተጠናቀቁ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዉ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የፕሮጀክቱ አንድ አካል በሆነዉ ቀቤና ልዩ ወረዳ የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አቶ ዳዊት ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳዉ ከዚህ በፊት በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ እና አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ምልክታ ያደረጉት ሀላፊዉ፤ በተያዘዉ በጀት አመት ለመገንባት ዉል መፈራረም መቻሉን ተናግረዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በበኩላቸዉ፤ በልዩ ወረዳዉ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ ጥያቄ እንደሚነሳ በመግለፅ ችግሩን ለመቅረፍ ከክልሉ ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተደረገ ያለዉ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አስተዳዳሪዉ ገልፀዋል።

የልዩ ወረዳዉ ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ከድር ደገፋ፤ የልዩ ወረዳዉ የህብረተሰብ ክፍሎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የልዩ ወረዳዉ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ሽፋን 28 በመቶ መሆኑን የገለፁት ሀላፊዉ፤ ከአገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ጋር ሲነፃፀር በቂ አለመሆኑን አመላክተዋል።

በተያዘዉ በጀት አመት ከልዩ ወረዳዉ አስተዳዳር እና ከክልሉ ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ዉሃ ችግር ለመቅረፍ ያግዛልም ብለዋል።

በመስክ ምልከታዉ የክልሉ ዉሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና የቀቤና ልዩ ወረዳ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን