ትምህርት ቤቶችን በትምህርት ግብዓቶችንና ቁሳቁስ ማደራጀት ለትምህርት ሥራ ውጤታማነት ያግዛል – ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ትምህርት ቤቶችን በትምህርት ግብዓቶችንና ቁሳቁስ ማደራጀት ለትምህርት ሥራ ውጤታማነት ያግዛል – ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ትምህርት ቤቶችን በትምህርት ግብዓቶችንና ቁሳቁስ ማደራጀት ለትምህርት ሥራ ውጤታማነት እንደሚያግዝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፣ ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የተገኙ ከፍተኛ አመራሮች በዳዉሮ ዞን የታርጫ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የሶሬ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለፁት፤ የትምህርት ሥራ ውጤታማነት እንዲረጋገጥ ለማስቻል ትምህርት ቤቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በትምህርት ግብዓት ማደራጀት ተገቢ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ይገኛል።

በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተሻለ የመማርና የማስተማር ሥራ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ለማስቻል የድጋፍና ክትትል ሥራም በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም አመላክተዋል።

የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ በሀገር ደረጃ ብቁ የተማረ የሰው ኃይል እንዲኖር የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በሚያስችል ተግባር ላይ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራም ውጤታማ እንዲሆን በተቀናጀ ጥረት ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ለታርጫ 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 25 ኮምፒውተሮችን እና ለሶሬ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጽሕፈት መሳሪያ ቁሳቁስ እገዛ አድርገዋል።

የክልሉ ማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ ለትምህርት ቤቶቹ በተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው ለትምህርት ሥራ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በየትምህርት ቤቶቹ መማሪያ ክፍሎችን፣ ቤተ መጻሕፍትንና ቤተ ሙከራዎችን፣ የኮምፒውተር መማሪያ ክፍሎችን፣ የምገባ ቦታዎችን፣ አድረው የሚያጠኑ ተማሪዎች ማደሪያን ጨምሮ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅቱ የተገኙ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆችና የትምሀርት አመራሮች በጉብኝቱ ደስታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ መሳይ መሰለ – ከዋካ ጣቢያችን