የከተማ መዋቅር ከተዘረጋ በኋላ በከተማዋ መነቃቃት መፈጠሩን የቱም ማጂ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

የከተማ መዋቅር ከተዘረጋ በኋላ በከተማዋ መነቃቃት መፈጠሩን የቱም ማጂ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም የከተማዋ ከንቲባ ገልጸዋል።

የዛሬዋ የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር የከተማ አስተዳደር መዋቅር ከመዘርጋቱ በፊት የማጂ ወረዳ ዋና ከተማ በመሆን በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር ቆይታለች። በእነዚህ ጊዜያትም በተለይም በከተማዋ የመሰረተ ልማት አለመሟላት ለስራ እንቅስቃሴ እንቅፋት ከመሆን ባለፈ ከተማዋ ካላት እድሜ አንጻር ያሉ ቤቶች ያረጁና ከተማዋን የማይመጥኑ እንደነበር ነው ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ማጂቀና ታደመ፣ አቶ ከድር ሰይድ፣ አቤት ተረፈ እና ያአቆብ አድማሴ የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ የከተማ መዋቅር ከተዘረጋ በኋላ በተለይም ያረጁ የከተማ ቤቶች እንዲፈርሱ ተደርገው በአዲስና ደረጃቸውን በጠበቁ ቤቶች ግንባታ መከናወኑ ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

መስራት የሚችሉ እና አቅም ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችም ቦታ ተረክበው ህንጻዎችን መገንባታቸው ለከተማው ትልቅ ለውጥ መሆኑንም ገልጸዋል።

የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እሸቱ አየለ በበኩላቸው፤ በማጂ ወረዳ ስር በማዘጋጃ ቤት አስተዳደር የነበረችው የዛሬዋ የቱም ማጂ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 2012 የከተማ አስተዳደር መዋቅር ማግኘቷን ይገልጻሉ።

ከተማዋ መዋቅሩን ካገኘች በኋላ በተለይም መልሶ የማልማት ስራ እየተሰራ ሲሆን በከተማዋ ያሉ ያረጁ እድሜ ጠገብ ቤቶችን በተሻለ ሁኔታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የመስራት አቅም ላላቸው ባለሀብቶች በማስተላለፍ ፎቆች እንዲገነቡ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ ያለውን የውሃ እጥረት ለመቅረፍ በፌደራል፣ በክልሉ፣ በዞኑ እና በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እየተገነባ ያለው የውሃ ፕሮጀክት 97 ከመቶ መጠናቀቁን ተናግረው፤ ይህም የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረትን ይቀርፋል ብለዋል።

በጤና ረገድም የማጁ ሆስፒታል የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ችግር እየፈታ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የመብራት አገልግሎትን በተመለከተ በሶላር በቱም አካባቢ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መሆን የተቻለ ሲሆን ማጂ አካባቢ ተጀምሮ ያልተጠናቀቀው ሲጠናቀቅ የመብራት ችግሩ ይቀረፋል ብለዋል።

ከተማዋ ወደፊት ብዙ የተሻሉ ተስፋዎች እንዳሏት የተናገሩት ከንቲባው፤ በተለይም በአካባቢው ያለው የወርቅ ሀብት በተገቢው መውጣት ሲጀምርና በአቅራቢያ ያሉ ትልልቅ የግሉ ኢንቨስትመንት ልማቶች በሙሉ አቅም ሲጀምሩ የከተማዋን የንግድ ስርአት ይበልጥ ከማሳለጥ ባለፈ ለከተማዋ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከተማ አስተዳደሩ ቦታ አዘጋጅቶ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ መጥተው ለሚያለሙ ባለሀብቶችም በሩ ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከወዲሁ ያረጁ ቤቶችን በመለየት የማፍረስ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን