የኦዲት ግኝቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የህግ ተጠያቂነት ላይ በትኩረት መሰራት ይገባል – ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ

የኦዲት ግኝቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የህግ ተጠያቂነት ላይ በትኩረት መሰራት ይገባል – ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኦዲት ግኝቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የህግ ተጠያቂነት ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ጋር በመተባበር በየደረጃው ከሚገኙ የኦዲት ግኝት አስመላሽ ግብረ-ኃይልና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን የህዝብና የመንግስት ሀብት ከብክነት ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ከክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ጋር በተከናወኑ ተግባራት ተመላሽ ያልሆኑ የኦዲት ግኝቶች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።

የክልሉ የኦዲት አስመላሽ ግብረ-ኃይል ባከናወነው ተግባር ከ179 ሚሊየን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉንም ዋና አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

ቅንጅታዊ አሰራሮች ላይ ያሉ ክፍተቶችን በማረም የህግ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግና የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት አስፈፃሚው አካል በትኩረት መስራት እንደሚገባው አመላክተዋል።

በመድረኩ በክልሉ የኦዲት አስመላሽ ግብረ-ኃይል የተከናወኑና እንደ ማነቆ የተነሱ ጉዳዮች በጥናት የቀረቡ ሲሆን ለተነሱ አሳቦችም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በምክክር መድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ቃልአብ ፀጋዬ