በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከ121 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከ121 ሚሊየን 475ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ገልጿል።

መምሪያው ይህንን መሰብሰብ የቻለው 245ሺህ 551 አባላቱ መሆኑንም ጠቁሟል።

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ከአርባምንጭ ጤና መድህን አገልግሎት የ2016 ሪፖርትና የ2017 በጀት እቅድ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይፉ ዋናቃ በመድረኩ እንደገለጹት፤ የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች አስቀድመው በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ ያልተገባ የጤና ወጪ ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተው በዘርፉም በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ትግበራ በዞኑ በ2008 ዓ.ም በ 3 ወረዳዎች መጀመሩንና በ2011 በጀት ዓመት 77ሺህ 848 አባላትን ማፍራት መቻሉን ጠቁመው ግንዛቤን የማሳደግ ስራ በመሰራቱ በአሁኑ ወቅትም  245ሺህ 551 የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላትን በማፍራት 121ሚሊየን 475ሺህ 106 ሺህ ብር መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።

የመድሀኒት ችግርን ለመፍታትም ከአርባምንጭ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ከጋሞ ልማት ማህበር ጋር በመሆን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የመክፈል አቅምን መሰረት ያደረገ የክፍያ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ሁሉም ዜጋ ጤናውን እንዲያመርት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ እንዳሉት፤ በ2015/16 በተከታታይ ሁለት አመታት የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል በጋራ መስራት ይጠበቅብናል።

አገልግሎቱ አንዳችን ሌላችንን እንድንደግፍ የሚያደርግ ቢሆንም ከአሰራር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው ጉድለቶችን በማረም በዞኑ በጤናው ዘርፍ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥና የመድሀኒት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን