የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ የሀድያ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ገለጸ፡፡

የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና በስነ-ምግባር የታነፁ ባለሙያዎችን ማፍራት እንዲችሉ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም መምሪያው አስታውቋል።

በሀድያ ዞን 8 የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን የዘመን እና የኬኤን አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ሥራ አስኪያጆች አቶ ተስፋዬ መኔቦ እና አቶ ከተማ ኑኔ እንደገለፁት፤ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎችን በብቃት ማሽከርከር የሚችሉ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር በስነ-ምግባር ጭምር የታነፁና ተገልጋዮችን የሚያከብሩ ዜጎችን ለመፍጠር በተደራጀ የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ።

ሰልጣኞች የማሽከርከር ልምድና ብቃትን በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብና በተግባር ልምምድ በቂ ዕውቀት ቀስመው ብቁ መሆን እንዲችሉና ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ከመከላከል አንፃር የራሳቸውን ድርሻ በአግባቡ መወጣት እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

እንደ ተቋማቱ ሥራ አስኪያጆች ገለጻ፤ ሠልጣኞች የተግባር ልምምድ ሜዳ የተመቻቸ ባለመሆኑ ችግር እየገጠማቸው እንዳለ አንስተው በሆሳዕና ከተማ የተጀመረው የትራንስፖርት ኮምፕሌክስ ግንቦታ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የሀድያ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመቀ በዶሬ እንደተናገሩት፤ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት በተሟላ ሁኔታ ማሰልጠን እንዲችሉ በቂ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

ከማሰልጠኛ ሜዳ ጋር በተያያዘ ፕሮግራም ተመቻችቶላቸው ባለው ቦታ የተግባር ስልጠና እንዲሰጡ እየተደረገ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ከመፍታት አንፃር በክልሉ እየተገነባ የሚገኘው የትራፊክ ኮምፕሌክሱ ተጠናቆ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በየዓመቱ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ በመከላከል ረገድ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደመቀ በየደረጃው የማጣራት ስራና የብቃት ማረጋገጫ ምዘና በየጊዜው  ይሰጣል ብለዋል።

በትራፊክ ቁጥጥር ዘርፍ ህግን የማስከበር ስራ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ የተቀናጀ ጠንካራ ክትትል በማድረግ ውጤት የሚያመጣ ተግባር መፈፀም ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን