ወደ ውጭ ለስራ ለሚሰማሩ ሰራተኞች እየተሰጠ ባለው ስልጠና ብቃታቸውን የሚያጎለብት ዕውቀት ማግኘታቸውን ሰልጣኞቹ ገለፁ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 10/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ወደ ውጭ ለስራ ለሚሰማሩ ሰራተኞች እየሰጠ ባለው ስልጠና ብቃታቸውን የሚያጎለብት ዕውቀት ማግኘታቸውን ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡

የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ በዚህ አመት ከ11ሺህ በላይ ሰራተኞችን ለማሰልጠን አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ የሰው ሀይል ልማት ፈፃሚ አቶ በሀይሉ አለሙ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት ወደ ውጭ ለስራ ለሚሰማሩ ከ1ሺህ 500 በላይ ሰራተኞችን መሰልጠናቸውን ጠቅሰው በተያዘው በጀት አመትም ከ11ሺህ በላይ ሰራተኞችን ለማሰልጠን ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል። 

አቶ በሀይሉ አክለውም ከዚህ ቀደም የነበረው የምዝገባ ሂደት ኦንላይን ባለመሆኑ ይዘገይ እንደነበር አንስተው አሁን ላይ ችግሩ መቀረፉንም ጠቁመዋል።

በኮሌጁ የሆቴልና ቱሪዝም አሰልጣኝ መምህር አቶ አበበ አክለው በበኩላቸው፤ ለሰልጣኞች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠናዎችን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው ወደ ውጭ ለስራ የሚሄዱ ሰራተኞች ኮሌጁ ያመቻቸላቸውን እድል መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ሳተላይት ካምፓስ ስልጠና ጨርሰው ሰርተፊኬት ለመውሰድ ከመጡ ሰልጣኞች መካከል የሺሀረግ ታዬ፣ ሰሚራ ሁሴን እና ሀምድያ በድሩ በሰጡት አስተያየት፤ ከልብስ ማጠብ ጀምሮ እስከ ምግብ ማብሰል የተግባር ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሰው ይህም በራስ መተማመንን እንደሚጨምርላቸው ተናግረዋል።

ሰልጣኞቹ አክለውም ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ከመሰደድ ተቆጥበው መንግስት ባመቻቸላቸው እድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

  ዘጋቢ፡ አስፍር ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን