የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ገቢዎች ቢሮ ከፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዳዉሮና ኮንታ ገቢዎች መምሪያ ለሚገኙ ባለሙያዎች የሥልጠና መድረክ ተዘጋጅቷል።
በሥልጠናው የተገኙ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የደንበኛ አገልግሎት የታክስ አወሳሰንና አሰባሰብ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንዱ ታደሰ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የገቢ ተቋማት ዘመናዊና በኤሌክትሮኒክ የታገዘ የገቢ አሰባሰብ ሂደት ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በማኑዋልና የእጅ በእጅ ሽያጭ የነበረውን የደረሰኝ አሰጣጥ ሂደት በማስቀረት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ ዘመናዊና ቀላል የታክስ አስተዳደር ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል ተብሏል።
ይህም በQR CODE የተመዘገበና የተረጋገጠ የማኑዋል ደረሰኝ በኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ እንደሚተካና ከታህሣሥ 30 ጀምሮ የታክስ ሪፖርት ከየተቋማቱ በማኑዋል ሳይሆን በE-tax ሥርዓት ይቀርባል ተብሏል።
ይህ ሂደት በቀጣይ ከግል ድርጅቶች ጋር የነበረውን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመላክቷል።
ከየካቲት 1 ጀምሮ በክልሉ ሁሉም የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት በአንድ የአሠራር ሥርዓት በመታገዝ ወጥ አካሄድ እንዲኖር ይሠራል ተብሏል።
በበጀት ዓመቱ በደረሰኝ ከሚሰበሰበው ገቢ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ እንዲቻል ግብ ተጥሎ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በደረሰኝ አሰባሰብ ላይ በሚፈጠረው ችግር ሕገወጦች ያልተገባ ጥቅም እንዳያገኙ በተቀናጀ ርብርብ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘመናዊና ቀላል የታክስ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ሕጋዊ ግብር ከፋዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላልም ተብሏል።
በደረሰኝ ገቢን በተገቢው መሰብሰብ ከንግድ ትርፍና ከጋራ ገቢ ማግኘት የሚቻለውን እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው።
በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የጅማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የታክስ መረጀና ሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ይልማ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር ክልሎችን በመደገፍ የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጠቃሜታ ያለውን ዓላማን በማንገብ ፍትሃዊና ዘመናዊ የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ ሥርዓት በማስፈን ጥራት ያለውን መረጃ በማደራጀት ተግባራትን በተገቢው ማከናወን ይገባቸዋል ብለዋል።
ደረሰኝ የማይኖር ከሆነ ገቢ እንደማይኖር ታሳቢ በማድረግ በገቢ ዘርፍ የሚከናወን ተግባር በትኩረት ሊከናወኑም ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
የበጋ መስኖ ልማት ተግባር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት የሚያደርገው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የሀድያ ዞን አስተዳዳር ገለጸ
በዳውሮ ዞን የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ የምክክር መድረክ ተካሄደ
በጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ በኮረሪማ ምርት ከሚለማው 8ሺህ 860 ሄክታር መሬት 50ሺህ ኩንታል ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ