የኦሮሚያ ክልል አጀንዳ አቅራቢዎች በየተወከሉበት ማህበራዊ መሠረት ምክክር እያደረጉ ነው
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኦሮሚያ ክልል አጀንዳዎችን በተወካዮቻቸው አማካይነት ለመቀበል በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የአገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ በክልሉ ካሉት 356ቱ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
እነዚህ ከ7 ሺህ በላይ የሆኑ የወረዳ ህብረተሰብ ተወካዮች የ10 ማህበረሰብ ክፍሎችን ውክልና የያዙ ናቸው።
ከማህበረሰብ መሠረቶቹ መካከል የንግዱን ማህበረሰብን ጨምሮ፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የተፈናቃዮች እና የሴቶች ማህበራት ይገኙበታል።
በየቡድናቸው በመሆን ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብላቸው በሚፈልጉት አጀንዳዎች ዙሪያ ያለአንዳች የሀሳብ ገደብ ሲመክሩ ተመልክተናል።
ወደ 48 የሚደርሱ ሞደሬተሮች (አመቻቾች) እና የኮሚሽኑ ሠራተኞች የምክክርና የውይይት ሂደቱን እያስተባበሩ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችም በየማህበረሰብ ክፍሉ በቡድን እየተወያዩ የሚገኙ ተወያዮችን እየተዘዋወሩ ምልከታ በማድረግ ላይ ናቸው።
ምክክሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ሲንከበላሉ የመጡ የፖለቲካ እና የማህበራዊ መስተጋብር ችግሮች የሚፈቱበትን እድል የሚፈጥር እንደሆነ የምክክሩ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
በተላይም ለሁሉም ነገሮች ቁልፍ መሠረት የሆነውና የመላ ኢትዮጵያዊያን አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ ለዘለቀው የሰላም ጥያቄ ምላሽ ያመጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም በመግለፅ።
ዘጋቢ፡ ጌታሁን አንጭሶ

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ