ለ5ኛው ጊዜ ለሚከበረው የጋርዱላ ህዝቦች የባህልና የፊላ ፌስቲቫል በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 08/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለ5ኛው ጊዜ ለሚከበረው የጋርዱላ ህዝቦች የባህልና የፊላ ፌስቲቫል በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጋርዱላ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል።

የዞኑ ማህበረሰብ በዓሉ በሠላም እንዲከበር የበኩሉን እንዲወጣ መምሪያው ጥሪ አቅርቧል።

የጋርዱላ ዞን ህዝቦች ከጥር ወር ጀምሮ በአንድነትና በአብሮነት የሚያከብሩት የባህልና የ “ፊላ” ፌስቲቫል በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ አዳነ ለገሠ ተናግረዋል።

በዞኑ ማህበረሰብ ዘንድ የጋራ ዕሴት ከሆኑት አንዱ የባህልና የፊላ ፌስቲቫልን ለማክበር የአካባቢው ተወላጆችን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችም በዓሉን በሠላም መታደም እንዲችሉ ከፀጥታ አካላት ጋር ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በጋርዱላ ዞኑ የሚገኙ አራት ነባር ብሄር ብሄረሰቦች አንድነታቸውንና አብሮነታቻውን ከማጠናከራቸው ባሻገር ዕሴቶቻቸውንና ባህሎቻቸውን ይበልጥ የሚያስተዋውቁበት በዓል መሆኑንም አስረድተዋል።

በጋርዱላ ህዝቦች ዘንድ ለ5ኛ ጊዜ የሚከበረው ይኸው የባህልና የፊላ ፌስቲቫል ክብረ በዓል በድምቀት እንዲከበር በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ ናቸው ብለዋል አቶ አዳነ።

ማህበረሰቡ በዓሉን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ተክብሮ እስከሚጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ እንጃ ገልሲሞ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን