የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ምርጥ ተሞክሮዎችን ማስፋፋት ተገቢ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ቢሮ አስታውቋል።
በጌዴኦ ዞን የአምራች አርሶ አደሮች ምርጥ ተሞክሮና የኩታ ገጠም የቡና ልማት ሥራዎች በጎፋ ዞን አርሶ አደሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተጎብኝቷል፡
በጉብኝቱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከ2 መቶ 28ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ ምርት እየሰጠ የሚገኘው 1 መቶ 64 ሺህ ሄክታር ብቻ ነው፡፡
ቀሪው 1 መቶ 24 ሺህ ሄክታር መሬት ባረጁና በበሽታ በተጠቁ ቡናዎች የተሸፈነ መሆኑን የገለፁት አቶ አማኑኤል የአምራች አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሪ አቅም ከፍ ለማድረግ ያረጁና በበሽታ የተጠቁ ቡናዎችን ነቅሎ በአዳዲስ ዝርያዎች በመተካት የቡናን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
የተሻለ ልምድ ያላቸውን አምራች አካባቢዎችን በመለየት ተሞክሮዎችን የማስፋፋት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ በቱማታ ጭራቻ ቀበሌ 26 ነጥብ 6 ሄክታር በክላስተር እየለማ ያለውን የቡና ማሳ ከክልሉ ከጎፋ ዞን የመጡ አርሶ አደሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች በመጎብኘት ተሞክሮ እንዲወስዱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ከዞኖች የተውጣጡ አርሶ አደሮች በዞኑ ያለውን የቡና አመራረት እንቅስቃሴን በመጎብኘት የአካባቢውን አምራች አርሶ አደሮች ልምድ ቀስመው መመለሳቸውንና በክልሉ መሰል ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት የአምራች አርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻልና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም ከፍ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡
በጌዴኦ ዞን በነበራቸው አጭር ቆይታ ብዙ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ማግኘት እንደቻሉ የተናገሩት ከክልሉ ጎፋ ዞን የመጡ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች፤ ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎችን በአዳዲስ ዝርያዎች በመተካት ቀሪ አካባቢዎች ለተሞክሮ ወደ እነሱ እንዲመጡ የሚያስችለውን ሥራ በቁርጠኝነት እንደሚያከናውኑ አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብረሰናይ ድርጅቶች ሚና የጎለ እንደሆነ ተገለፀ
ተቀራርቦ በጋራ መሥራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያዝ ተጠቆመ
የጀፎረ ባህላዊ አውራ መንገድን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተጠቆመ