በዓለማችን ለ33ኛ፣ በሀገሪቱ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን “ዊማ ኢንተርናሽናል” ከተሰኘ ግብረስናይ ድርጅት ጋር በመተባበር “የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታች እና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በበዓሉ ወቅት የተገኙት የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዝናቡ ዋኖሬ፤ በልዩ ወረዳው ዊማ ኢንተርናሽናል ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አካል ጉዳተኞች የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዳይሆኑ ከማድረግ ጀምሮ በተለያዩ አደረጃጀቶች ግንዛቤ በመፍጠር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አካል ጉዳተኝነት እንዴትና መቼ እንደሚመጣ አይታወቅም ያሉት አቶ ዝናቡ፤ አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ ከመላክ ጀምሮ በተለያዩ አስፈላጊ ነገሮች ልንደግፋቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
አቶ ሙላቱ ሾሞሬ በዊማ ኢንተርናሽናል የሙዱላ ፊልድ ኦፊስ ማኔጀር እና ወ/ሮ ትርንጓ ድጉኖ በድርጅቱ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችና የስርዓተ ጾታ ዘርፍ አስተባባሪ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የበዓሉ መከበር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን አመላክተዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፋንቱ ዳምጤ ተቋሙ ከአጋር ድርጅቶችና በልዩ ወረዳው ከሚገኘው “ሰው ለሰው በጎ አድራጎት ማህበር” ብሎም ሌሎችም የመንግስት ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን በቅርብ ጊዜ ተቋቁሞ ከክልሉ መንግስትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት ወ/ሮ ትዕግስት ሉበጎ የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይና የማህበራዊ ችግሮች መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው።
እንደክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከላትና የአስፈላጊ ግብዓቶች ድጋፍ ጭምር እየተሰራ ነው ያሉት ወ/ሮ ትዕግስት፤ በተለያዩ አዋጆች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን አንስተው፤ ሁሉም በተለያዩ ማህበራዊ ምክንያቶች የተደበቁ አካል ጉዳተኛ ወገኖችን አደባባይ በማውጣት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ መሐመድ ሸይቾ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለ አካል ጉዳተኝነት የነበረ ኋላ ቀር አመለካከት እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በሁሉም አካባቢዎች እኩል ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
አንዳንድ ያነጋገርናቸው የበዓሉ ተሳታፊ አካል ጉዳተኞች በበኩላቸው፤ እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍና እንክብካቤ ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመው ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።
በዓሉ ዘንድሮ በዓለም ለ33ኛ፣ በሀገሪቱ ለ32ኛ ጊዜና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/