እጅን የመታጠብ ልምድና ባህል እንዲዳብር እየተሠራ ነው – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) እጅን የመታጠብ ልምድና ባህል እንዲዳብር እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

“ንጹህ እጆች ለጤናችን ዋስትና ናቸው” በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ የዓለም አቀፍ የእጅ መታጠብ ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ሐሩ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከብሯል።

የይርጋጨፌ ወረዳ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ተካልኝ በቀለ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ ቀናቶቹ በሚከበሩበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ዘወትር ንጽህናችንን ከጠበቅን በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻልና ከመከላከል በተጨማሪ አክሞ የማዳን ሥራም እየተሠራ ስለመሆኑ አመላክተዋል።

የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ማሞ በበኩላቸው፤ የእጅ መታጠብ ቀን የጤናውን ጎል ለማሳካት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በወሳኝ ሰዓቶች እጆችን መታጠብ የጨቅላ ህጻናትን ሞት 44 በመቶ፣ የተማሪዎችን መጠነ መቅረትና ማቋረጥን 30 በመቶ፣ 23 በመቶ የመተንፈሻ አካላት ላይ የሚመጡ በሽታዎችን፣ የተቅማጥን በሽታዎችን 47 በመቶ እና በንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን የሚከላከል መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።

ለዚህም ከ40 እስከ 60 ሰኮንዶች እጃችንን በተገቢው መታጠብ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ እንዳሉት፤ እጃችን ከየትኛውም የሰውነት አካላችን ይልቅ ለበሽታ አምጪ ተዋሲያን ተጋላጭ በመሆኑ 80 በመቶ የሚሆኑ ጀርሞች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በእጅ አማካኝነት ነው።

እጅን በውሃ እና በሳሙና መታጠብ ተላላፊ በሽታዎችን የሚከላከል እንደሆነ ያሚያመላክቱት አቶ መና ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የእጅ መታጠብ ልምድና ባህል እንዲዳብር ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሁሉም ህብረተሰብ እጅ መታጠብን ልምድና ባህል እንዲያደርገውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል “መጸዳጃ ቤትን በንጽህና መያዝና መጠቀም ዘመናዊነት ነው” በሚል መሪ ቃል የመጸዳጃ ቤቶች ቀንም በክልሉ እየተከበረ ስለመሆኑ አቶ መና አመላክተዋል።

ዘጋቢ: እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን