በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓዝ የነበረ 57 በርሜል ቤንዚን መያዙን በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ፖሊስ አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓዝ የነበረ 57 በርሜል (12,540 ሊትር) ቤንዚን መያዙን በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ፖሊስ አስታወቀ።
መድረሻውን ወደ ኣሪ ዞን ጂንካ ከተማና ደቡብ ኦሞ ዞን ቀይ አፈር ከተማ አድርጎ ሲጓዙ ከነበሩ ሁለት አይሱዙ መኪናዎች 57 በርሜል ህገወጥ ቤንዚን በፖሊስ ድንገተኛ ፍተሻ መያዙን የማሌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አማን ኢሳያስ ለደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ተናግረዋል።
በኮድ3-B69036 አ.አ እና ኦሮ ኮድ3-65780 አይሱዙ መኪናዎች የተጫኑ 57 በርሜል (12,540 ሊትር) ቤንዚን መድረሻውን ጂንካና ቀይ አፈር ከተማ በማድረግ ሲጓዝ እንደነበር ተገልጿል።
ታህሳስ 03/2017 ዓ.ም የማሌ ወረዳ ፖሊስ የሌሊቱ ድንገተኛ ቁጥጥር በማድረግ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ በማሌ ወረዳ ቦሽኮሮ ቀበሌ ቤንዚን የጫኑ መኪናዎችን ከአሽከርካሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር ማድረግ መቻሉን የማሌ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አማን ኢሳያስ አስታውቀዋል።
ከህገወጥ የቤንዚን ንግድ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ፖሊስ ከከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ጋር ብርቱ ቅንጅት ፈጥሮ እየሰራ እንደሚገኝ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አማን ገልፀው፤ በቀጣይም ይህንን ተግባር በይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉና ማህበረሰቡም መሰል ህገወጥ ጉዳዮች ሲያጥሙት ጥቆማ በመሰጠት ህገወጥነትን እንዲከለከል ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ በቁጥጥር ሥራው ላይ ለተሰማሩት ፖሊስ አባላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ህዝቡንና የሀገሪቱን መንግሥት የሚጎዱ ህገወጥ ንግድንና መሰል ተግባር ለመከላከል በሁሉም አካባቢ ፖሊስ በኃላፊነት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘገቢ፡ ጄታ ታገሠ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ በማስተዋወቅና በማላመድ ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተገለፀ
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደትና የጥምቀት በዓላትን ህብረተሰቡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ ነው-የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ
በሽታን በመከላከልና ተገቢ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ