የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግብና መጠጦችን ባለመጠቀም ህብረተሰቡ ጤንነቱን መጠበቅ እንዳለበት ተገለፀ

በቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር የምርት ቁጥጥር እና አስወጋጅ ግብረ ሀይል የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶችን አስወግዷል።

የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ የሆኑት በቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ዩኒት መሪ አቶ ተረፈ ጳውሎስ፤ ነጋዴው እና ሸማቹ ህብረተሰብ ምግብ እና ምግብ ነክ ነገሮችን ሲሸጥም ሆነ ሲገዛ የተመረተበትን እና አገልግሎቱ የሚያበቃበትን ጊዜ በአግባቡ በማየት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የግብረ ሃይሉ አባል እና የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ ረዳት ኢንስፔክተር ረዳኸኝ በዙ በበኩላቸው፣ የፖሊስ ተግባር አደጋ ከመድረሱ በፊት መከላከል ስለሆነ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እየተከታተልን የማስወገድ ሥራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግብና ምግብ ነክ ነገሮችን በተጠቃሚው ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርሱ እየተከታተሉ እንደሚያስወግዱ የተናገሩት ደግሞ የከተማ አስተዳደር ማህበራዊ ክላስተር ጤና ዩኒት ውስጥ የበሽታ መከላከል ቡድን መሪ አቶ አብቦሸ ወልዴ ናቸው።

ህብረተሰቡ የታሸጉ ምግቦችን እና መጠጦችን ሲጠቀሙ የተመረተበትን እና አገልግሎቱ የሚያበቃበትን ቀን የማየት ልምዱ ያልዳበረ ስለሆነ ለቀጣይ ተከታታይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ለመስራት እንዳቀዱ አቶ አብቦሸ አክለው ተናግረዋል።

የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው በርካታ የፋብሪካ ወተት እና የለስላሳ መጠጦችን የግብረ ሃይሉ አባላት በተገኙበት የማስወገድ ስራ ተሰርቷል።

ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን