ህዝቡ በግብርና ልማት ሥራዎች የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኣሪ ዞን አስተዳደር ገለፀ

“የምርታማነት እምርታ ለቤተሰብ ብልፅግና በአዲስ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ግብርና መምሪያ ወቅታዊ የግብርና ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የኣሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተሰፋዬ በንግግራቸው ግብርና የህዝባችን ትልቁ አቅምና ሀብት ብሎም የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ባለድርሻ አካላት ዘርፉን በማገዝ ለመጣው ውጤት አመስግነው ውጤቱ ለቀጣይ ረጅሙ ጉዞአችን በር ከፋች ነው ብለዋል።

አክለውም በየጊዜው ለምንስራው የግብርና ሥራዎች ብልፅግናን ለማረጋገጥ መላውን ህዝብ በማሳተፍ በመስኖ ልማት፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እና ሌሎችም የልማት ሥራዎች በተያያዥነት የሚፈፀሙ ሲሆን መድረኩም እስከ ታችኛው መዋቅር በንቅናቄ እንደሚመራ ገልጸዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በመክፈቻ ንግግራቸው የድሽታ ግና በዓልን ዘንድሮ በልዩ ሁኔታ በአንድነትና በአብሮነት ባከበርንበት ማግስት የምናደርገው መድረክ በመሆኑ ለቀጣይ የግብርና ሥራዎች ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

አክለውም የበጋ ወራት የመስኖ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እና በሌሎችም የግብርና ሥራዎች የህዝቡ ተሳትፎ በአስተሳሰብና በተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀሪ የግብርና ሥራዎች ላይ አመራሩ ክትትሉን በማጠናከር በወቅታዊ የትኩረት መስኮች ህዝቡን በማሳተፍ መስራትና በተለይም የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጫ የሆነው የሌማት ቱሩፋት ሥራዎቻችንን ማስፋት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመድረኩ የመወያያ መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በሰነዱ መነሻ ተሳታፊዎች የተለያየ ጥያቄና አሰተያየት አንስተዋል።

የመድረኩ መሪዎችም ተግባራትን በዕቅድ በመምራት በሁሉም ዘርፍ በስኬት የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስቀጠል በጉድለት የታዩ አፈፃፀሞችን በፍጥነት ለማረም ቅንጅታዊ አሰራርን በመከተል ቴክኖሎጂን በማስፋት በመደጋገፍ ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን