ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ወሳኝ ነው – የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ወሳኝ መሆኑን የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ ገለፀ፡፡

በኮሬ ዞን ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ኮሬና አካባቢ ፕሮግራም ከኮሬ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጋር በመተባበር ከዞን፣ ወረዳና ከኬሌ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንዳባ እንደተናገሩት፤ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ የሚከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደርገው ጥረት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው በመሆኑ ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር የሚቻለው ከብክለት የፀዳ አካባቢ ሲኖር ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፤ በተፈጥሮ የተሰጠንን ሀብቶች በመጠበቅና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ሲሉ ገልጸዋል።

የኮሬ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ዩኒት አስተባባሪ ወ/ሮ በኃይሏ አሸናፊ በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመቋቋምና ለመከላከል የደን ልማትን ማስፋፋትና የደን ሽፋንን መጨመር አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።

በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ባለሙያዎች ወደ ማህበረሰቡ በመውረድ የወሰዱትን ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ ግንዛቤ እንዲፈጥሩና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሙሴ መንገሻ፣ አቶ ስምኦን ስንታየሁ እና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት፤ ከስልጠናው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተፈጥሮን የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት የሁላችን እንደሆነ ተረድተን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ተቀናጅተን መስራት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን