ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በመንግሥትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በቴሌቶን ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ እያዳረገ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ  አስታውቋል።

የፎንቆ ከተማ ከተቆረቆረች ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረች ብትሆንም የዕድሜዋን ያህል ለውጥ ሳይታይባት እንደቆየች ይነገራል።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ እየታየ ያለው  የልማት እንቅስቃሴ በጥሩ ጅምር ላይ እንደሚገኝ ነው የከተማ ነዋሪዎች  የተናገሩት።

በከተማዋ የተጀመሩ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የወጣቶች መዝናኛ ቦታዎች ስራ አበረታች በመሆናቸው  ተጠናክረው መቀጠል እንደለባቸውም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር፣ የመብራት መቆራረጥና መሰል የልማት ሥራዎችም በዘርፉ ባለድርሻ አካላት በኩል ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ የአገልግሎቶች ጽ/ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ አበበ በበኩላቸው የዉሃና የመብራት ጥያቄዎች በመንግስት ብቻ የማይፈታ  በመሆኑ የከተማውን ህብረተሰብ በማስተባበር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ የመንገድ ዳር መብራት ተደራሽ ለማድረግና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም ለማሽነሪ ግዢ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ከህዝብ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን እስካሁንም ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ አቡቴ በበኩላቸው ከተማዋ በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ያሉባት እንደመሆኑ የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራዎችን  ደረጃ በደረጃ  ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከተማው ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ፍላጎቱ ያላቸው ባለሀብቶች በመረጡት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀረቡት ከንቲባው እንደ መንግስት መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል።

“አንድ ከተማ አንድ ፕሮጄክት” በሚል መሪ ሀሳብ በመንግሥትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በቴሌቶን ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ እየተዳረገ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል::

የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚፈታው የከተማውን የውስጥ ገቢን በተገቢ በመሰብሰብ ነው ያሉት ከንቲባ የውኃና የመብራት መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት ከክልል ጋር በመነጋገር ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን